ነገረ መለኮት (Theology)

<<Theology >> የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት ማለትም ‹‹Theo›› እና ‹‹logy›› የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ Theo›› ማለት ‹‹God›› ማለት ሲሆን ‹‹logy›› ደግሞ study or knowledge የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው፡፡ በመሆኑም ‹‹Theology›› (የነገረ መለኮት) ማለት ስለ እግዚአብሔር የማይጨበጠውን፣የማይላጠውን፣ የማይገመተውን እንዲሁም ከሰዎች አእምሮ በላይ የሆነውን ጌትነቱንና አምላክነቱን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው መጠን ሰዎች የሚረዱበት ጥበብ ነው፡፡

እግዚአብሔር ተብሎ ወደ ግዕዝ የተተረጉመው በዕብራይስጡ ቋንቋ ኤል ወይም በብዙ ቁጥር ኤሎሄም የሚለው ቃል ነው፡፡ ኤል ማለት  ኃይል ማለት ነው፡፡ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሌሎች የእግዚአብሐር ስሞችም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህዌ ማለት የነበረ ያለና የሚኖር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል ወደ አማርኛው ሲተረጎም የሀገር  ወይም የዓለም ጌታ ማለት ነው፡፡ በምድራችን ላይ በርካታ ሃይማኖቶች፤ እምነቶችና አመለካከቶች የመኖራቸውን ያህል ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረና (ያስገኘ) እና የየዕለት ሁኔታዎችን  የሚመራ እና  የሚቆጣጠር አንድ ከሰዎች በላይ የሆነ የማይታይ ትልቅ ኃይል ያለ መሆኑን አብዛኛው ወገኖች ይስማማሉ፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሃይማኖት የራሱ የሆነ መመሪያና ትምህርት አለው፡፡

በዚህ መሰረት የክርስትና ነገረ መለኮት  ስንል ስለ እግዚአብሔር ህልውና ስለጠባዮቹ ስለመለኮታዊ አንድነቱ ሶስትነቱ ለፍጥረቱ ስለሚያደርገው ጥበቃ (መግበቱ) ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ዓለምን ማዳኑንና በአጠቃላይም ለዚህ ሁሉ ትምህርት ምንጭ በሆነው አምላካዊ መጽሀፍ የተገለጸው ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚመረምር ትምህርት (ዕውቀት) ማለታችን ነው፡፡

መሆኑም በዚህች አጭር ፅሁፍ ውስጥ ይህንን ሀሳብ በስፋት ለማየት አባይን በጭልፋ ያህል ከባድ ስለሆነ በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርዶቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን አስተምሮ በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

 

ሀልወተ እግዚአብሔር

ለእግዚአብሔር ህላዌ ማስረጃነት ከሚቀርቡት በርካታ ጉዳዮች መካከል በተለይ የፍጥረታት ሥነ ሥርዓትና አሠራሩ፣ የህሊና ምስክርነት ፣የሠው ልጆች የተፈጥሮ ዝንባሌ፣ የቃለ እግዚአብሄር፣ የታሪክ ምስክርነት ወዘተ….. ይገኙበታል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ወፎችንና እንስሳትን ብትጠይቋቸው ብዙ ሊያስተምሯችሁ በቻሉ ነበር፡፡ በምድር ላይ እና በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረቶች ጥበብ እንዲያስተምሯችሁ ብትጠይቋቸው ሁሉም እግዚአብሔር አንደሰራቸው ያስረዱአችኋል፡፡ የፍጥረቶቹን ሕይወት የሚመራ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ነፍስ በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ነው፡፡›› (መ.ኢዮ 12÷7-10) በማለት ዓለምን ያስገኘ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል፡፡ መዝሙረኛው ቅ/ዳዊትም ይህንን ሀሳብ ሲያጠናክረው ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔር ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይ ጠፈሮችም የእግዚአብሔር ሥራ ያውጃሉ፡፡›› (መዝ19፡1) በማት ከእግዚአብሔር ውጭ ይህች ዓለም ሌላ አዛዥና ባለቤት እንደሌላት ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡

በአንድ ወቅት በአቴና ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ስለ እግዚአብሄር ሀልወት ለማመንና ለመቀበል ተቸግረው መስዋዕት እያቀረቡ መስዋዕት የሚያቀርቡለትን አምላክ ባለማወቃቸው ‹‹ ለማይታወቅ አምላክ›› ብለው ጽፈው ሲያመልኩ ግን የሚያመልኩትን አምላክ ሳያውቁ እንደነበረ ሀዋርያው ቅ/ጳውሎስ አርዮስፋጐስ በተባለው ሥፍራ ቆሞ የክርስትናን ሃይማኖት እንዴት እንደሰበካቸውና የማይታወቀውን አምላክ ሲገልጽ ‹‹ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሠማይና የምድር ጌታ ነውና….›› (የሐዋ 17፡24) በማለት ስለእግዚአብሔር ሀልወት ለአቴና ሰዎች ገልጧል፡፡

 

የእግዚአብሔር ጠባዮች

የእግዚአብሔር ጠባዮች በሁለት  አጠቃለን ለማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በማናቸውም መልኩ ለእግዚአብሄር እንጂ ለፍጡር የማይነገር የእርሱ የብቻው የባሕርይው መገልጫዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በማንኛውም ሁኔታ ውሱንነት የሌለው መሆኑ፣ በራሱ የሚኖር መሆኑ፣ የማንም እርዳት የማያስፈልገው መሆኑ፣ ዘለዓለማዊነቱ አለመለወጡ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑ አለመታየቱ፣ አልፋና ኦሜጋ መሆኑ ወዘተ የመሰሉት ጠባዮች ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው ይህም ሁሉን ዐዋቂነቱ፣ ጥበበኛነቱ፣ ሁሉን ቻይነቱ፣ ቅዱስነቱ፣ ትክክለኛ ዳኝነቱ፣ ፍቅሩና ደግነቱ፣ እውነተኛነቱና ታማኝነቱ…. ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ሰዎች በጸጋ በተለያየ መጠን ያግኙ  እንጂ የእግዚአብሔር ግን የባሕርይው ናቸው፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ

የክርስቲያን ሃይማኖት ከሌሎች ሃይማኖቶች ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ዋንኞቹ ርዕሶች መካከል ምሥጢረ ሥላሴ ወይም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት እምነት አንዱ ነው፡፡ በክርስትና እምነት መሰረት እግዚአብሄር አንድ ነው አንዱ አምላክ ሦስት አካል አለው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት አካል አለው ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል አንድ መለኮት ሦስት አካል፣ ወይም ሦስት አካል ያለው አንድ መለኮት ማለት ነው፡፡ የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት ምስጢር ግልጽ ሆኖ በመጽሀፍ ቅዱስ ተቀምጧል፡፡ ሊቀነቢያት ሙሴ በጻፈው በመጀመሪያ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል ‹‹እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› ( ዘፍ 1፡1) በማለት አንድነቱን ገልጾ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን በአምሳያችን እንፍጠር ( ዘፍ 1፡26) በማለት በአንድ ምዕራፍ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ (ዘፍ 3፡22 ፣ ዘፍ 11፡7፣ ኢሳ 6፡3፣ ዘኑ 6፡24)

ከመጀመሪያው ጀምሮ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ስለአንድነት እና ስለሦስትነት ትምህርት ግልጥ ሆኖ በስም ቀርቧል፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማቴዎስም እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፡፡ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኃቸው የኔ ደቀመዛሙርት አድርጓቸው›› (ማቴ 28፤19) በማለት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተጽፎ የሚገኘውን የሦስትነቱን ምስጢር በግልጽ በስም ጠቅሶ ይገኛል፡፡(ማቴ 3፡13-17 ፣ ማር1፡19-11፣ ሉቃ 3፡21-22፣ ማቴ17፡5፣ሉቃ 1፡35፣ዮሐ1፡33)

በተለያየ ዘመናት በነገረ መለኮት ላይ ለሚነሱ ክህደት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የትምህርቱ ስርወ እምነት እንዳይበረዝ በተለይ በኒቂያና በቁስጥንጥንያ ጉባዔያት የሐይማኖት ቀኖናዎች የአንድነቱን፣ የሦስትነትን እምነት አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ፀሎተ ሃይማኖት በሚባለው የሃይማኖት ጸሎት ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡

‹‹ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሄር አብ፤ ‹‹ከዘመናት ሁሉ በፊት ከአብ የተወለደ በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሔር ወልድ ‹‹ሕይወትን በሚሠጥ ጌታ፣ ከአብ ከሰረፀ፣ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› ይህንን ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቀኖናቸው ደንግገዋል፡፡

 

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብር

በንጉስ ቁስጢንጢኖስ ዘመነ መንግስት በ325 ዓ.ም በኒቅያ ከተማ በተሰበሰቡት 318 የዓለም ኤጲስ ቆጶሳት ውሳኔ መሰረት ከተወገዘው ከአርዮስ ጀምሮ የጌታችን የባሕርይ አምላክነትና ከአብ ጋር ያለው እኩልነት የሚክዱ የአርዮስ ወገኖች ነበሩ አሁንም አሉ፡፡ ለዚህም ምላሽ ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስ ስንኳ ያለእርሱ የሆነ የለም›› (ዮሐ1፡3) በማለት ስለክርስቶስ ክብር ተናግሯል፡፡ ይህም ማለት (ዘፍ1፡1) ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በእነርሱ የሚገኙትን ፍጥረቶች ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር እርሱ ነበር ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ እውራንን ያበራ፣ አንካሳን ቀጥ ያደረገ፣ ዱኩማንን ከድካማቸው ያሳረፋቸው፣ ሙታንን ያስነሳ፣ ህሙማንን የፈወሰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ነቢያት እንደተናገሩት፣ ሃዋሪያት እንደሰበኩት መምህራን እንዳስተማሩት ይልቁንም ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እንዳረጋገጠልን ይህንን የሐይማኖት መሰረት አድርገን እናምናለን፡፡ ‹‹የሥጋን ህማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ እግዚአብሔር በባህርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም ሕማም በሚስማማው ባህርዩ ኃይልን እንጂ ሞትም ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትን አጠፋ ከሞተም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ›› (ሃይ አበ.ገጽ 175) ቅዱስ ቴዎድጦስ የዕንቁራ ኤጲስ ቆጶስ፡፡

 

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር

መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መሆኑን ቤተክርስቲያን ታምናለች (ታስተምራለች) ይህም ማለት በባህርይ በጠባይና የመለኮት ግብር በሆኑ ነገሮች ሁሉ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንዱ ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ ሳይሆን ሦስቱም አካላት በከሃሊነት፣ በክብር በሥልጣን፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እኩል ናቸው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ እኩል መሆኑን ቅዱሳት መጻህፍት በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጠዋለሁ፡፡ በቅዱሳት መጻህፍትም በግልጥ የቀረበ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አካልነት ማለት ከሶስቱ አካላት አንዱ መሆኑን ታምናለች፡፡ ይሁን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር የሚክዱ መናፍቃን በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ እንደ አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና መቅዶንዮስ ያሉ ናቸው፡፡

ለእነዚህም መናፍቃን ሊቃውንት ‹‹ወንአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማህየዊ ዘሠረፀ እመ አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሆ ምስለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ……›› በማለት በሃይማኖት ፀሎት ደንግገዋል፡፡ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል፡፡ (1ቆሮ 12፡11) በማለት የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር ገልጧል፡፡ ከላይ ለማየት እንደተሞከረው በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያለመጠራጠር ለልጆቿ የሥላሴን አንድነትና ሶስትነት ያለመቀላቀል ያለመለያየት ስታስተምር ኖራለች ወደፊትም ታስተምራለች፡፡

የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን!!!