“ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምእ”(የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ)
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
በቤተክርስቲያናችን የቃለ እግዚአብሔር አሰጣጥ መሠረት ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ኖላዊ ተብሎ ተሰይሟል፡፡
ኖላዊ ተብሎ በሚጠራው ሰንበት “ኖላዊ ዘመጽአ…” የሚለው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት በሌሊት የአገልግሎት ክፍለ ሰዓት በሊቃውንቱ ሲዘመር ያድራል፡፡ በጧቱ በሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት (ዕብ.13÷16)፣ (1ጴ 2÷21)፣ (የሐ.10÷36-43 በዲያቆናትና በካህኑ በንባብ ይቀርባል፡፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፣ዮሴፍን እንደመንጋ የምትመራ፣ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ የሚለው የዳዊት መዝሙር (መዝ 79÷1) በዲያቆኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ (ዮሐ 10÷1-22) በካህኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ ቃሉም እንዲህ ይነበባል፡፡
“አማን አማን እብለክሙ ዘኢቦአ እነተ አንቀጽ ውስተ አጸደ አባግዕ ወአርገ እንተካልእ ገጽሰራቂ ወፈያት ወጉህልያ ውእቱ”
“እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፡፡ በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል፡፡የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል፡ ፡የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፡፡ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፡፡ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና፡፡ .. እኔ የበጎች በር ነኝ….በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ ይድናል፡፡
….መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹ የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፡፡
በግ
በግ ሥጋው ለመስዋዕትነትና ለምግብ፣ ጠጉሩና ቆዳው ደግሞ ለልብስ የሚሆን የዋህ የቤት እንስሳ ነው (ዘፍ 4÷2) (ዘሌ 22÷19) (ዘፀ 14÷13) በግ በተለይ ለፋሲካ መስዋዕት ይታረድ ነበር (ዘፀ 12÷3) ስለዚህ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአበሔር በግ ተብሏል፡፡ (ዮሐ1÷29) (ራዕ 5÷6)በግ ንጹሕና የማይጎዳ የዋህ እንስሳ ስለሆነ ሐሰተኞች የዋህ ለመምሰል የበግ ለምድ በሚለብሱ ተመስለዋል፡፡ (ማቴ 7÷15)በጎች ክርስቶስን የሚከተሉ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡(ማቴ 25÷33)
እረኛ
በጎችንና ፍየሎችን ከብቶችንም የሚያሰማራ እረኛ ተብሎ ይጠራል፡፡ (መዝ 23÷2)እረኛ የጠፋውን ይፈልጋል፡፡ (ሉቃ 15÷3) ከአውሬዎችም ይጠብቃል(1ሳሙ 17÷34)
እረኛ ኃላፊነት ላለባቸው ሁሉ ምሳሌ ነውና፣ ሕዝብን የማይጠብቁ ባለስልጣኖች ከባድ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ (ኤር23÷1)፣ (ሕዝ34÷1)
በበሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር እረኝነት የተነገረው ሁሉ በአዲስ ኪዳን ለክርስቶስ ተነግሯል፡፡ ይህም ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ፈሪሳውያን ዕውር መሆናቸውን ተናግሮ እንደጨረሰ ስለመልካም እረኛ ማስተማር ጀመረ፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው የአይሁድ መሪዎች የእስራኤል ጠባቂዎች እረኞች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ መሪዎች ይህን ሀላፊነት መወጣት አልቻሉም፡፡ ዕውሮችና ምንም ነገር የማያውቁ ሆኑ (ኢሳ 56÷9)ሐሰተኞች፣ በበጎች በር የማይገቡ፣ ሌቦችና ወንበዴዎች ሆኑ፡፡
እውነተኛ እረኛ የሆነው ከርስቶስ ሁል ጊዜ በበሩ ይገባል፡፡ በብሉይ ኪዳን እራሱ እግዚአብሔር የእስራኤል እረኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ (መዝ 23÷1) ፣ (ሕዝ34÷15) ኢየሱስ ክርስቶስ እረኛችን ነው፡፡ እርሱም ከእርሱ በታች ሌሎች እረኞችን ሾሟል፡፡ (የሐ 20፣17)ክርስቶስ ሕይወቱን ለበጎች አሳልፎ የሰጠ መልካም እረኛ ነው፡፡
ቅጥረኛ እረኛ ግን ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፡፡ በየትኛውም ዘመን ከቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል ቅጥረኛ የሆኑ እረኞች አሉ፡፡ እነዚህ እረኞች መንጋውን አያስቀድሙም፡፡ አንድ ችግር በመጣ ጊዜ መንጋውን በትነው ይሸሻሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በጎቹን ያውቃል ፣ ደግሞም በጎቹን ይወዳል፡፡ በመሆኑም ስለበጎቹ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡