ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋል ሉቃ.2÷11

                                          በመ/ር ኃይሉ እና ዘሩ

4.1

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቀን አቆጣጠር ቀመር አሁን በ2ዐዐ5 ዓ.ም የምናከብረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ዘመን 2ዐዐ5 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

እግዚአብሔር አዳምን በ7ኛ ቀን ሔዋንን ደግሞ በ14ኛ ቀን ከፈጠረ በኋላ በገነት እግዚአብሔር አምላካቸውን እያመሰገኑ እንዲኖሩ ቢያስቀምጣቸው እነርሱ ግን ባለመታዘዝና ወደ መመራመር በመግባት ከእግዚአብሔር ተለይተው ከገነት በመውጣት እሾህና አሜኬላ ወደምታፈራው ምድር ወርደው እንዲኖሩና ከእነርሱ የተገኙት ልጆቻቸውም የዚህ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ተበይኖባቸዋል፡፡ አዳምም ታሪክ እንደሚነግረን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም የሳጥናኤልን ጥበብ ማለፍ አቅቶት ሳይሳካለት በመቅረቱ እግዚአብሔር ጥረቱን ተመልክቶ ወደ ተባረርክበት እና ወዳሰብክበት ገነት መግባት ቢያቅትም አንተ ድል መንሳት ባቃተህ ሥጋ ተዋሕጄ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው በማለት ቃል ገብቶለታል፡፡ ከዚህ ቃል ኪዳንም የተነሳ የአዳም ልጆች እና ልጅ ልጆች አቤቱ እጅህን ከአርያም ልከህ አድነን፣ ጨለማችን ይብራ፣ እስራታችን ይፈታ ይበጠስ እያሉ ያለቅሱ ይጮኹ ነበር፤ በየዓመቱም ሱባኤ በመቁጠር እየፆሙ ይፀልዩ ነበር፡፡ እርሱም የነቢያት የአባቶቻችንን ጩኸት በመስማት ቀኑ በደረሰ ጊዜ የሸክሙን ቀንበር፣ የአስጨናቂውን ዘንግ፣ ለመስበር፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተዘረጋውን የጠብ ግርግዳ ለመቅረፍ፣ በጨለማ ለሚኖረውም ሕዝብ ብርሃን ለመስጠትና ለመሆን፣ ነቢያት የናፈቋትን የማዳኑን ዕለት ለማሳየት በሉቃስ ወንጌል እና በሌሎቹም ወንጌላት ላይ እንደተጠቀሰው በእንግድነት ለቆጠራ በሄዱበት በዳዊት ከተማ

በቤተልሔም ተወለደ፡፡ ወቅቱ ሮማዊያን ግዛታቸውን አስፋፍተው ኢየሩሳሌምንም ይገዙ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ለግብር አከፋፈል እንዲመች እና እንዲሁም ግዛታቸውን እንደገና ለማጠናከር እንዲያስችላቸው በዚያ ወራት ከአውግስጦስ (ከ31 ዓ.ዓ – 14 ዓ.ም) ቄሳር ሁሉም እንዲቆጠር ትዕዛዝ ወጣ፡፡ ቄሬኔዎስም የሶሪያ አገረ ገዥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት የመጀመሪያ ጽሕፈቱ አድርጎ ሁሉም እንዲቆጠር በመታዘዙ ሁሉም ወደ ተወለደበት ቦታ ሄዶ መቆጠር ግድ ስለሆነ ዮሴፍም የትውልድ ቦታው ቤተልሔም በመሆኑ በአውግስጦስ ቄሳር ትዕዛዝ መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ቤተልሔም ሄደ፡፡ ቤተልሔም ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በሕዝብ ብዛት የተጨናነቀች እና ሁሉም ቀድመው ሥፍራ የያዙ በመሆኑ የእንግዳ ማረፊያ ቦታዎች ተይዘዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ዮሴፍና እመቤታችን ማረፊያ ሥፍራ ባለማግኘታቸው ለጊዜው የሚጠለሉበት ቦታ ፈልገው ያገኙት ቦታ በከብቶች ማደሪያ ሥፍራ ላይ ስለሆነ በዚያው ቆይታቸውን እያደረጉ ባሉበት የእመቤታችን የመውለጃዋ ጊዜ ደርሶ ስለነበር በዚያው የበኩር ልጇን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው በከብቶች ማደሪያ ግርግምም አስተኛችው፡፡ ጌታም የትህትና መምህር ስለሆነ ዓለም ቦታ ባትሰጠዉም በሌሎች ተይዟል ብላ ሥፍራ ብታሳጣውም እርሱ ግን እኛን ለማስተማር ጌታ ነኝ ይህ አይገባኝም ሳይል በማይገባው በከብቶች በረት ተኛ፡፡ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ጌታ ዙፋኑን ትቶ ለሰዎች ልጆች ፍቅር ብሎ ከውርደታችን ሊያነሳን በተዋረደው በከብቶች ማደሪያ ተወለደ፡፡ ጌታችን የተወለደበት ምክንያት

 

1. በአዳም የገባውን ቃልኪዳን ለመፈፀም

2. በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል የለውን የጠብ ግርግዳ ለማፍረስ

3. የሰው ልጆችን የጨለማ ሕይወት ለመገርሰስ ነው

ጌታ የወለደበት ሥፍራ ቤተልሔም ሲሆን ቤተልሔም የሚለው ሥያሜ ካሌብ መጀመሪያ አዙባ የምትባል ሚስት አገባ ነገር ግን ከጠላቶቹ ወገን ስለነበረች በእርስዋ አልሰየማትም ቀጥሎ ከብታ የምትባል ሚስት አገባ በእርሷም ከብታ ተብላለች ቀጥሎ ኤፍራታ ወንድ ልጁን ወለደ ስሙንም ልሔም አለዉ ልሔም ማለት ኀብስት ማለት ነዉ፡፡ ቤተልሔም ማለት ቤተ ኀብስት ማለት ሲሆን ቤተ የእመቤታችን ኀብስት የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ሲወለድ ሰብዓ ሰገል በቤተልሔም ተገኝተው ስጦታ በመስጠት ሰግደውለታል ሰብዓ ሰገል ማለት የዕውቀት ሰዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የእሩቅ ምሥራቅ ስዎች ሲሆኑ አባታቸው ዥረደሽት ይባላል ፈላስፋም ነው፡፡ አንድ ቀን ውሃ አጠገብ ሆኖ ወደ ሰማይ ሲመለከት ድንግል በሰሌዳ ኮከብ ተስላ ሕፃን ታቅፋ ሲያይ ፈጥኖ በብረት ሰሌዳ ቀርፆ ሲኖር በመሞቻው ወቅት እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡ ብሎ ነግሮአቸው ስለነበር ኮበቡ ጊዜው ሲደርስ በመውጣቱ እነዚያ ጠቢባን ሰዎች ተመልክተው በኮከቡም በመመራት ወደ ቤተልሔም በመምጣት ወርቅ ከርቤ ዕጣን አበርክተውለታል፡፡

ወርቅ የተበረከተለት ምክንያት

1. ወርቅ የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላ ሃላፊያን ናቸው፡፡ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ

2. ወርቅ ንፁሕ ነው አንተም ንፁሕ ባሕርይ ነህ ሲሉ ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው፡፡ ወርቅ ንፁህነቱ የሚታወቀው በእሳት ሲፈተን ነው የሃይማኖትም ንፁህነቱ የሚታወቀው መከራ ሲቀበሉበት ነው፡፡

ዕጣን የተበረከተለት ምክንያት

1. ዕጣን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ

2. ዕጣን ምዑዝ ነው መዐዛው ያማረ ነው ያንተ ማዕዛም የባህርይ ነው ሲሉ ባንተ ያመኑም ምዕመናን ሃይማኖት እና ምግባራቸው ማዓዛ ነው፡፡

ከርቤ

1. አንተ የማታልፍ ነህ በሰውነትህ ግን መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፡፡

2. ከርቤ የተሰበረውን ልብ ይጠግናል የተለየውን አንድ የደርጋል አንተም በመሞትህ ከማኀበረ መላዕክት የተለየውን አዳምን እና ልጆቹን አንድ ታደርጋለሁ፡፡

3. ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው ምዕመናኑም በፍቅር አንድ ይሆናሉ በማለት ከርቤ አበርክተውለታል፡፡ ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ወርቅ ዕጣን ከርቤ አበርክተውለታል፡፡ በቤተልሔም በጌታ መወለድ ተለያይተው የነበሩት ማኀበረ መላዕክትና ሰዎች ከ5ሺ ዘመናት በኋላ አብረው ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ በማለት ምስጋና አቅርቧል፡፡የጌታችን የልደት ቀን ለሰዎች ልጆች መዳን መሰረት የተጣለበት ቀን በመሆኑ የደስታ ቀን ነዉ፡፡ በመሆኑም መላእክት እና እረኞች በአንድነት እንዳመሰገኑ እኛም የምስጋና ቀን በማድረግ እግዚአብሔርን ሰብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ በማለት የጌታ መወለዱን በማሰብ ተሕትናን በመላበስ በጎ ነገር በማድረግ እናክብር መድኃኒት ለሰላማችን ተወልዶልናልና ይህን የምሥራች እንድንናገር ስለታዘዝን ይህን ታላቅ ዜና አየተናገርን ልናከብረዉ ይገባል፡፡መልካም በዓል፡፡