ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመምህር ዘለዓለም ወንድሙ የሥጋ ዕረፍት አስመልክተው ጥልቅ ኀዘናቸውን ገለጹ

ወአርአይከኒ ፍኖተ ሕይወት
የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤
መዝ 16÷11
– አንተ መንገዴ ሆነህ ወደ ሕይወት እንዳቀና አደረግኸኝ
– በመንገድነትህ የደረስኩበት ሕይወት አንተ ነህ።
መምህር ዘለዓለም ወንድሙ ለወንጌል የተሰጡ የሕይወት መንገዳቸውን በወንጌል ተልዕኮ ላይ ትኩረት በማድረግ የመሩ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ለምናደርግላቸው የአገልግሎት ጥሪ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በታዣነት በትጋት ያገለገሉ ልጃችን ነበሩ::
መምህር ዘለዓለም ወንድሙ በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ለአገልግሎት እየተጠሩ የሚመጡ ብቻ ሳይሆኑ በራሳቸው ተነሳሽነት እና ከልባቸው ርኅራኄ በመነሳት በችግር ውስጥ ለሚወድቁ ምዕመናን ከልብ የሚጨነቁ ድጋፍም የሚያደርጉ ነበሩ። በተለይ በስልጤ ዞን በቅበት ከተማ በእምነታቸው ምክንያት በጽንፈኞች ከመንደራቸው ተፈናቅለው በቡታጀራ ደብረ ጽዮን ቅ/ማርያም ቤ/ክ ተጠልለው ለነበሩ ካህናት እና ምዕመናን በአካል ተገኝቶ ከማጽናናት ባለፈ ከውጪው አለም ገንዘብ በማስባስብ ከተጎዱት ጎን የቆሙ ነበሩ።
በመጨረሻም በመምህር ዘለዓለም ወንድሙ ድንገተኛ የሥጋ ዕረፍት የተሰማንን ልባዊ ኀዘን እየገለጽን እግዚአብሔር የወልደ ሰማዕትን ነፍስ በዕቅፉ ያሳርፍልን ።
አባ ሕርያቆስ
የአዲስ አበባ የሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ