ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በቅዱስ ፓትርያርኩ 13ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት
“ ወምክሆሙ ለውሉድ አበዊሆሙ – የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው።”(መጽሐፈ ምሳሌ 17፥6)
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ እንኳን ለ13ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላም አደረስዎ፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን በተናገረው በዚህ ታላቅ የጥበብ ቃል ውስጥ “አባቶች” የሚለው ቃል ሥልጣንን፣ ጥበቃን፣ ማንነትን እና የሥነ ምግባር መሠረትን ይወክላል። የእውነተኛ ልጅ ክብር ሀብት፣ ሥልጣን ወይም ሌላ ደረጃ አይደለም፡፡ የልጆች ክብር አባቶች ናቸው፡፡ አባቶች የሥነ ምግባር መመሪያ፣ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ደህንነት እና ፍቅር የሚሰጡ ሆነው ተገልጠዋል፡፡
እግዚአብሔር እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፣ ለልጆችህም አስተምረው በማለት ያዘዘው ትእዛዝ በአባቶች የሚፈጸም ነው (ዘዳግም 6፡6-7)፡፡ የቅንና ታማኝ አባት መኖር ጠባቂ የማግኘትና በሥርዓት የመተዳደር ዋስትና ነው፡፡ ስለዚህ የጠቢቡ ቃል በትውልዶች መካከል ያለና በቅብብሎሽ የሚቀጥል የጋራ ክብርን ያመለክታል፡፡
በአባቶችና በልጆች መካከል ጠንካራ ትስስርና ቅርበት አለ፡፡ አበው ያስተምራሉ፣ ከተሳሳተ መንገድም ይመልሳሉ፡፡ መንፈሳውያን አባቶች በሃይማኖት የልጆቻቸው ክብር ናቸው፡፡ በተመሳሳይ፣ ፓትርያርክ ደግሞ ርእሰ አበው (የአባቶች አባት) የሁላችንም አባት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዛሬ 13ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን እያከበርን የምንገኘው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የጳጳሳት፣ የካህናትና የምእመናን ሁሉ አባት ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የራሷን ፓትርያርክና ጳጳሳት መሾም እስከጀመረችበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ጉዳዮች ተሟልተው ይገኙ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከግብጽ የሚመጡትና ላለፉት አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት የመሩት ጳጳሳት በቋንቋ፣ በባሕልና፣ በሀገራዊ ዘይቤዎች ውሱንነት ነበረባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን ያህል እንዳታድግና እንዳትሰፋ ሆና ቆይታለች፡፡ ዛሬ ያ ጊዜ አልፎ እነሆ የስድስተኛውን ፓትርያርክ 13ኛ ዓመት በዓለ ሢመት እያከበርን እንገኛለን፡፡ ለዚህም ሁሉን የሚችል የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
በራሳችን ሲኖዶስና ፓትርያርክ መመራት የቻልንበት ይህ ታላቅ የነጻነት ዕድል በቀላሉ የተገኘ አይደለም፡፡ ሁሉም የሚያውቀውና ታሪክ ዘግቦ የያዘው ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ስለዚህ በተገኘው ዕድል የመጡ ትሩፋቶችን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ፣ እንደ ቃለ ዐዋዲ የመሳሰሉ ሕግና ደንቦች፣ የሰበካ ጉባዔ መደራጀትና ከአህጉረ ስብከት እስከ አጥቢያ ድረስ ያሉትን መዋቅሮች ልንጠብቃቸውና ልናጠናክራቸው ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ፓትርያርክ ብሎ መጥራት አርእስተ አበው ከሚባሉት ከአብርሃም፣ ይስሐቅ ያዕቆብና ከ12ቱ ነገደ እሥራኤል አባቶች የተነሣ መሠረት አለው፡፡ እነዚያ እግዚአብሔር በሰጣቸው ቃልኪዳን መሠረት ሕዝብን ሲመሩና ሲያስተዳድሩ የነበሩ አባቶች ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት ላይ የተሠራው የፓትርያርክ ሥልጣን ከሁሉ የላቀና ከጌታችንና አምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ መንፈሳዊ ሥልጣን ነው፡፡ አጠቃቀሙ የበለጠ አድጎ የታየው ከዓለም አቀፍ ጉባኤያት በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱም በየጉባዔያቱ የተገኙና አንጸባራቂ ሚና የነበራቸው አባቶች ፓትርያርክ በሚል መጠሪያ ተጠርተዋል ወይም እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡
የፓትርያርክ ሥልጣንና ሚና ሃይማኖትን በአንድነት ለመጠበቅ፣ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ለማረጋገጥና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ቅዱስ ሔሬኔዎስ ጸረ መናፍቃን በሚሰኘው ሦስተኛ መጽሐፉ በዚህ ደረጃ የምንቆጥራቸው ሐዋርያት የሾሟቸውን ጳጳሳትና ከእነርሱ ቀጥለው በቅብብሎሽ አሁን ድረስ ያሉትን ፓትርያርኮች እንደሆነ አስተምሯል፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስም የቤተ ክርስቲያን አንድነት መሠረት ፓትርያርኩ መሆኑን በመልእክታቱ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ዛሬም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጌታችን የመሠረተውና ከሐዋርያት የተነሣ ቅብብሎሽ ሳይቋረጥ የደረሰን ለመሆኑ ማረጋገጫ ምልክት ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትም እንደ ጽኑ መሠረት ናቸው፡፡
ባለፉት 13 ዓመታት ቅዱስነታቸው በመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም የሚበጁ በርካታ ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡ በውሳኔዎቹ መሠረትም ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ የትምህርት ተቋማት እንዲጠናከሩ፣ የልማት እንቅስቃሴዎችም በሰፊው እንዲከናወኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ ቅዱስነታቸው በሾሟቸው ጳጳሳት የክህነት አገልግሎት በመላዋ ኢትዮጵያ ተዳርሷል፡፡ አሁንም እየተከናወኑ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችና የግንባታ ሂደቶች አሉ፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን በኢኮኖሚም ለማጠናከር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አካል ነው፡፡
የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ሁሉ ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የተከናወኑ አይደሉም፡፡ ይልቁንም በብርቱ ፈተናዎች ውስጥ በትዕግስትና በጥበብ ማለፍ የሚቻልበትንም የአመራር ጥበብ በቅዱስ አባታችን ዐይተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷ ጸንቶ እንዲቀጥል ይተጋሉ፡፡ በየአጽዋማቱና በዓላቱ በሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ሰላምን፣ አንድነትንና ፍቅርን ይሰብካሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከቃላቸው ተምረዋል፣ ተመክረዋል፣ እንዲሁም ተጽናንተዋል፡፡
ቅዱስ አባታችን ባላቸው ጠንካራ የሃይማኖት ሰብእና እና የጸሎት ሕይወት በሌላ እምነት ሰዎች ሳይቀር እጅግ የሚወደዱ ናቸው፡፡ ይህም በተለየ ጥበብ ከመምራትና ከማስተዳደር በተጨማሪ አርአያነት ያለው ሕይወታቸውም አስተማሪ ነው፡፡ በመሆኑም ነገ ከሚጠብቁን ታላላቅ ተግባራት አንጻር የቅዱስነታቸው አመራር ባለ ተስፋዎች ያደርገናል፡፡
ከተሠሩት በላይ ሌሎች መንፈሳዊና ዘርፈ ብዙ ልማታዊ ሥራዎች በሰፊው እንደሚሠሩ እናምናለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስነትዎን በሕይወት በጤና ይጠብቅልን!
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰኝ፣
አባ ሳዊሮስ
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ
ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡
