ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ የተለያዩ መዛግብትና ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ይዘት እንዲቀይር ለተቋቋመው ኮሚቴ የሥራ መመሪያ ሰጡ

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተለያዩ መዛግብትና ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ይዘት እንዲቀይር ለተቋቋመው ኮሚቴ የሥራ መመሪያ ሰጡ፡፡
በብፁዕነታቸው መመሪያ መሠረት በመንበረ ፓርትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃውን የጠበቀ የግቢ የማስዋብ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ግቢውን ከማስዋብ ጎን ለጎን አላስፈላጊ ዕቃዎች ቦታ እንዲይዙ፣ በመጋዘን ውስጥ ለዘመናት ተከማችተው የነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የተለያዩ መዛግብትና ሰነዶች ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሰነዶች የጠቅላይ ቤተክህነቱን፣ የሊቃውንቱን እና በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች የተጻፉ ታሪኮች፣ ውሳኔዎች የያዙ ናቸው፡፡
እነዚህን ሰነዶች ዘመኑ በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወደ ዲጂታል መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ ብፁዕነታቸው ይህን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ኮሚቴ አዋቅረው፣ በየዕለቱ መመሪያ እየሰጡ፣ አፈጻጸሙን እየተከታተሉ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ለገበያ እንዲበቁ፣ ሰነዶቹም ለጥናትና ምርምር ምቹ ሆነው እንዲቀመጡ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ይህንንም ሥራ የሚሠሩ ወይም ፋይሎቹን ወደ ዲጂታል የሚቀይሩ ባለሙያዎች ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት መካከል የተመረጡ ናቸው፡፡ ሠራተኞች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት በአጭር ጊዜ ሥራቸውን እንዲሠሩ የሥራ መመሪያ በብፁዕነታቸው ተሰጥቷል፡፡ ሠራተኞች በሦስት ዐይነት የሥራ ዘርፍ የሚሠማሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ እነዚህም፡- የመጀመሪያው ፋይሎች የሚያደራጁ፣ ሁለተኛው ፋይሎችን በየመልካቸው የሚለዩና በሦስተኛ ደረጃ መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት ኖሯቸው በሚሰጣቸው የዲጂታል ሥልጠና ታግዘው መዛግብቱንና ፋይሎቹን ወደ ዲጂታል የሚቀይሩ ናቸው፡፡
ብፁዕታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ግቢውን የማስዋብ ማስተካከል የተጀመረው ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በመጋዘን ውስጥ የተጠራቀሙ መጻሕፍትና ሰነዶችን በማውጣት ቦታ እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ያለንበት ዘመን የቴክኖሎጂ በመሆኑ እነዚህን ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት ይዘታቸውን ሳይለቁ ደረጃቸውን ጠብቀው አርካይቭ (ዲጅታል) ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፋይሎች የቀደሙት አባቶች የደከሙበት፣ የተለያዩ ታሪኮችን የያዙ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
“እስከ አሁንም ዲጂታላይዝድ አለማድረጋችን ዘግይተናል” ያሉት ብፁዕነታቸው “ሥራው ከፍተኛ ጥረትና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ በፍጥነት የተሻለ ሥራ እንድትሠሩ፤ በዚህ ሥራ የተሳተፋችሁ ሁሉ ባለ ታሪኮች ናችሁ፤ እንደ ራሳችሁ ሥራ አድርጋችሁ እንድትሠሩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም ሥራዎቹ ማለቅ አለባቸው፡፡” ሲሉ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሥልጠናውም በቅርቡ እንደሚጀመር ኮሚቴው ገልጿል፡፡
©EOTC TV