ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት በሆሣዕና አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሚማሩ 26 የአብነት ተማሪዎች ሥልጣነ ክህነት ሰጡ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለተ በሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ፀሐይ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በማሕበረ ቅዱሳን ዋናዉ ማዕከልና በሆሣዕና ማኅበረ ቅዱሳን ፣ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የገጠሪቷ ቤተክርስቲያን ለመጡ ለ26 አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።ማዕረገ ክህነት የተቀበሉት አገልጋዮች በሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እየተማሩ የቆዩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በዛሬዉ ዕለት ማዕረገ ክህነት ሊቀበሉ ሲመጡም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ መመሪያ ሰጭነት በሀገረ ስብከት ደረጃ ተፈትነው ያለፉ መሆናቸዉን የሀገረስብከቱ የካህናት ክፍል ለሚዲያ ክፍላችን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዛሬው ዕለተ 4 ዲያቆናት የቅስና እንዲሁም 22 ደቀ መዛሙርት የዲቁና ማዕረግ ተቀብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ክህነት ለተቀበሉ አገልጋዮች ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ብፁዕነታቸዉ በአባታዊ ቡራኬያቸዉ እግዚአብሔርን በመፍራትና በቀና ልብ ሆኖ ማገለገል እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡ ሲሆን ፣የተቀበሉትን የክህነት ክብርና ሕይወት በሥርዓትና በአግባብ እየተመላለሱ መጠበቅ እንደሚገባቸውም በአባታዊ ቡራኬያቸዉ መክረዋል።
የአብነት ተማሪዎቹም ለ2 ዓመት በሆሣዕና መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የማሕበረ ቅዱሳን የአዳሪ ትምህርት ቤት እየተማሩ መቆየታቸዉ ይታወቃል።
