የአየር ጤና መካነ ስብሐት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የሠራቸው G+2 የቢሮ ሕንጻና የተለያዩ የልማት ሥራዎች በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ተመረቁ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ስር የሚገኘው የአየር ጤና መካነ ስብሐት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረት በቅርብ ዓመታት ቢሆንም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።ከነዚህም በአጭር ጊዜ የተሠሩና ዛሬ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ የተመረቁት የተለያዩ ልማቶች G+2 ሕንጻ የአስተዳደር ጽ/ቤት፣ የግቢ ማስዋብ፣ የመጠለያና የቴራዞ ሥራ ፣ የጸበል ቤት እንዲሁም የመንገድና የድልድይ ሥራ ተጠቃሾች ናቸው።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ሐላፊዎች፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች፣ ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የደብሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ተማሪዎች እና ምእመናን ተገኝተዋል።
በደብሩ የተሠሩትን ሁለንተናዊ ልማቶችን አስመልክቶ በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር አማካኝነት ቀርቧል።
ምክትል ሊቀ መንበሩ ደብሩ በመሩት በቀድሞው አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ጽጌ ሐረገ ወይንና አሁን በማስተዳደር ላይ በሚገኙት በሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ መሪነት “አይሆንም_አትጀምሩት፣ አይሳካም_አትሞክሩት” የተባሉባቸውን ተግዳሮቶች ሁሉ በማለፍ እዚህ ለመድረስ ተችሏል ብለዋል።
የተሠሩት ሥራዎች ከ32_ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን በ10 ወራት ውስጥ የተሠሩ መሆናቸውን አስታውሰው በዚህም በከፍተኛ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን አደራ ብላ የሰጠቻቸውን የአባትነት ሐላፊነት በአግባቡ በመወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያስመሰግን ለውጥ ለማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ በበኩላቸው የልማቶቹ ሁሉ ምንጭና ጥንካሬ “ቅድሚያ_ለቅዱስ_ወንጌል_አገልግሎት” በሚል መርሕ በደብሩ የሚከናወኑ የተለያዩ የቅዱስ ወንጌል ጉባኤያት ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በሦስት ወንዝ በተከበበና በድልድይ ላይ ቤተ ክርስቲያን ከመሥራት አልፎ ግቢውን ለቅዱስ ወንጌል ምቹ የማድረግና በርካታ የልማት ሥራዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በመልአኩ ተራዳኢነት በማኅበረ ካህናቱና ምእመናኑ ድጋፍና ትብብር መልካም ውጤት ለማስመዝገብ ተሞክሯል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ አገልግሎት ድርሻቸው ሰፊ ለሆኑ ሁሉ ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ከደብሩ አስተዳዳሪ ጀምሮ ለማኅበረ ካህናቱ፣ ለምእመናኑ ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው በሞያቸው በገንዘባቸው ላገዙ ሁሉ የካባ ሽልማትና የእውቅና ምስጋና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ ተቀብለዋል።
በመቀጠልም መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ሐላፊ ትምህርተ ወንጌልና ስለቦታው ምስክርነት ሰጥተዋል።
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል የቦታው ትናንት ትንሽ ቢሆንም በወጣቶቹ አስተዳዳሪዎች በማኅበረ ካህናቱ አብሮነት በምእመናኑ ድጋፍ ዛሬ ላይ ለሌሎች አርአያ ሊሆን የሚችል ታላቅ ሥራ በመሠራቱ በእጅጉ አደንቃለሁ ብለዋል።
በትንሹ የሚከበር በትልቁም የሚመሰገን እግዚአብሔር ነውና በዚህ ቦታ የሆነውም ይሄው እውነት ነው ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በደብሩ የተሠሩ ልማቶችና ግቢው ከሰሙትና ከተነገራቸው በላይ በመሆኑ በእጅጉ መደነቃቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም የታላቁ የወንጌል ባለሟል፣ ሩቅ አሳቢ ባለራዕይ የነበሩት የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ካልዕ የመንፈስ ልጅ፤ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና የአስተዳዳር ደረጃዎች ያገለገሉት ሊቀ ካህናት ዕዝራ ንዋይ የደብሩ አስተዳዳሪ የመሪነት ድርሻቸውን ስለተጠው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል ብፁዕነታቸው።
የመጨረሻውን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡት ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቦታው በዚህ መልክ ቀንቶ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እዚህ ደረጃ በመድረሱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ደብር የተሠሩት ሥራዎች ሠሪውን ብቻ ሳይሆን ሿሚውንና ሀገረ ሰብከት እንዲሁም በቅርብ ከሰትትል የሚያደረገውን የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ሐላፊዎችንም የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም መርሐ ግብሩን በጸሎትና በቡራኬ ፈጽመዋል።
የአየር ጤና ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል የጥንታዊ የረፒ/ረቢ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የጸበል ቦታ የነበረ ሲሆን በኋላ ቤተ ክርስቲያን መተከል እንዳለበት ታምኖበት በሀገረ ስብከቱ ፈቃድ የተመሠረተና ዛሬ ላይ በብዙ አገልግሎት የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው።
