በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተባባሪነት እየተገነባ የሚገኘዉ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተባባሪነት እየተገነባ የሚገኘዉ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት በሆሣዕና ከተማ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተባባሪነት እየተገነባ የሚገኘዉ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ በሚፈለገዉ ልክ እየተከናወነ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሰብሳቢ መልአከ ገነት መምህር ቢኒያም መንቾሮ ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ሰብሳቢ መልአከ ገነት መምህር ቢኒያም መንቾሬ እንደገለጹት የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም የበላይ ጠባቂ፣አርቆ አሣቢነት ፣የተቋሙን ደረጃ ለማሳደግ ትውልዱን ለመታደግ ታልሞ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ቀን አንስቶ በሀገረስብከቱ ቁጥጥር አድራጊነት፣ ለፕሮጀክቱ የተዋቀሩትን ኮሚቴዎች በመቆጣጠር ፣አስፈላጊዉን ለግንባታዉ ሂደትም የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማቅረብና ክትትል በማድረግ ስራዎቹ እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ዲ/ን ኢንጂነር ለዓለም ጥላሁን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ እንደገለጹት የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም የG+5 ሕንጻ ፕሮጀክት በብፁዕነታቸዉ ብርቱ ድጋፍና ክትትል የሚገነባ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዉ፣ ፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት በሚፈለገዉ ልክ በተቀመጠዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስራዎች በጥራት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ አሁን ባለበት ደረጃ የቁፈሮ ስራዎች ተጠናቀዉ ፣የኮንክሪት ሙሌት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን አንስተዉ ፣ይህ ፕሮጀክት ለፍጻሜ እንዲደርስ የሁሉም አካል ድጋፍ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ይህ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታዉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ የቤተክርስቲያንን ዶግማ ሥርዐትና ትውፊት የጠበቁ 192 ደቀመዛሙርትን ተቀብሎ የሚያስተምርና በውስጡ የአብነት ትምህርት ቤት ያለው መሆኑንና ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን ፕሮጀክት በመደገፍ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ዲያቆን ኢንጅነር ለዓለም አሳስበዋል።
በመጨረሻም መልአከ ገነት መምህር ቢኒያም መንቾሬ በፕሮጀክቱ ላይ የብፁዕነታቸዉ ራዕይ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ለማስቀጠል፣ ታሪክና ትውፊት ሳይዛባ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ትምህርተ ሃይማኖትን ለማስፋፋት ፣የተዘጉ አቢያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት፣የገጠሪቷን ቤተክርስትያን የሚረከቡ ልጆችን ለማፍራት፣ የካህናት ማሰልጠኛዉን ደረጃ ማሳደግና ወቅቱ የሚጠይቀው ዋናው ተልዕኳችን መሆኑንም አስታውሰዋል። ሀገረ ስብከቱ የአብነት ት/ቤቶችን በማጠናከር፣ በማዘመንና በማስፋፋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዉ፣በዚህ ታሪካዊው ፕሮጀክት ላይ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን አሻራዉን በማኖር የአቅሙን ድጋፍ (በማቴሪያል፣በገንዘብ፣ በሃሳብ ) እንዲያደርግ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ላይ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ምዕመናን፣ በጎ አድራጊዎችና ባለሙያዎች ሁሉ ድጋፈቸዉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን ፕሮጀክት በመደገፍ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የፕሮጀክቱ ሰብሳቢ መልአከ ገነት መምህር ቢኒያም መንቾሬ አሳስበዋል።
እንደሚታወቀዉ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም የበላይ ጠባቂ እንዲሁም በሀገር ባህል ሽማግሌዎች ጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም መቀመጡ ይታወሳል።