አዲስ መንገድና ድልድይ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ቡራኬ ተመረቀ

የአያት መሪ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የሠራው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያስገባ አዲስ መንገድና_ድልድይ በዛሬው ዕለት በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ፣የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ፣ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ ሐላፊዎች፣ መልአከ ብፁዓን አእመረ በኩረ ጽዮን የደብረ አስተዳዳሪ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ምእመናንን ምእመናንት ተገኝተዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብፁዓን አእመረ በኩረ ጽዮን ለብፁዕነታቸው በቤተ ክርስቲያኑ እየተሠሩ የሚገኙትን ሥራዎችና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ያስጎበኙ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ በሦስት አቅጣጫ በሚባል መልኩ የግለሰቦች ይዞታ የሚያዋስነው በመሆኑ ምክንያት በስተምሥራቅ በኩል የሚገኘው አንድ መግቢያና መውጫ ብቻ የነበረው መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑን ከተመደቡበት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ይህንን ችግር ለመፍታት በማሰብ ከተለያዩ ከሰባካ ጉባኤው፣ ከሕንጻ ኮሜቴውና ከማኅበረ ካህናቱ ጋር ከተመካከሩ በኋላ በስተምዕራብ በኩል በሚገኘው ወንዝና በግለሰብ ይዞታ ላይ አዲስ መንገድና ድልድይ ለመሥራት ግለሰቦቹን ቦታ እንዲፈቅዱላቸው በመማጸን በእግዚአብሔር ቸርነት ግለሰቦቹ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ቦታን የቤተ ክርስቲያን መግቢያ መንገድ እንዲሠራ መፈቅዳቸውን አስተዳዳሪው አስታውሰዋል።
የተሠራው አዲስ መንገድና ድልድይ ለማስቀድስ የሚመጡ ምእመናን እግልት የቀነሰ፣ በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ተከራይተው ለሚገኙ አምራች ባለንብረቶች ሁነኛ መፍትሔ እንዲሁም ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታና ሌሎች በግቢው ውስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች በአጭር ጊዜ የፈነጠቀ የብርሃን መንገድ ነው በማለት ጥቅሙን አስረድተዋል።
የተሠራው አዲስ መንገድና ድልድይ ከሚመለከታቸው አካላት የተወጣጣ ኮሚቴ በማወቀር በፍጥነት የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንገዱና የድልድይ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ባቀረቡት ሪፖርት በበጎ አድራጊ የአካባቢው ምእመናን ጥረትና ትብብር እንዲሁም በአስተዳዳሪው ከፍተኛ ትጋት በ2 ወር ከ15 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
አዲሱ መንገድና ድልድይ 70 ሜትር ርዝመት በ10 ሜትር ስፋት እንደሆነና ከ4.3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት አብራርተዋል።
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር ወ/ሮ ማርታ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኑ በአካባቢው ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤልና ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቀጥሎ የተመሠረተ ቢሆንም ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግንባታና በልማት ሥራዎች አኳያ ግን እንደ ዕድሜው አለመሆኑን ተናግረዋል።
አክውም መልአከ ብፁዓን አእመረ በኩረ ጽዮን ከመጡ በኋላ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች በእጅጉ አመርቂና ውጤቱም የሚያጓጓ ነው ብለዋል።
ከነዚህም አለመጋባባት የነበረበትን የቦታ ይዞታና ኪራይ በስምምነት በመፍታት፣ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲወጣ በማድረግ እንዲሁም ዛሬ የተመረቀው አዲስ መንገድና ድልድይ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።
የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበርና የአዲስ መንገድና ድልድይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የደብሩ አስተዳዳሪ ላደረጉት አባታዊ ተግባርና ቤተ ክርስቲያናዊ ተልእኮ የከበረ ምስጋናችን እናቀርባለን ብለዋል።
በመጠልም የደብሩ ሰበካ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኑ ምሥረታ ወቅት ቦታውን በመስጠት ታሪክ ለሠሩ የአካባቢው ባለይዞታዎች ከ26 ዓመታት በኋላ እውቅናና ምስጋና ይገባቸዋል በማለት በብፁዕነታቸው እንዲባረኩና እንዲሸለሙ አድርጓል።
ለደብሩ አስተዳዳሪ ለመልአከ ብፁዓን አእመረ በኩረ ጽዮን በአጭር ጊዜ ለከናወኗቸው መልካም ሥራዎች የመቀደሻ ልብሰ ተክህኖ በስጦታ ተሸልመዋል።
በሌሎች የሥራ ዘርፍ ለተራዱና ለደገፉ የክብር ካባና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ትምርህርተ ወንጌል የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ “በልቧ ትጠብቀው ነበር” በሚል ርእስ ተነስተው ነገሮችን በትግስት በጥበብና በእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረትነት መፈጸም እንደሚገባ አስተምረዋል።
ክቡር ሥራ አስኪያጁ በእግዚአብሔር ያመነ አይደለም ንብረቱን ራሱን ይሰጣል ያሉት፤ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲመሠረት ቦታ የሰጡትን እንዲሁም ዛሬ የተመረቀው አዲስ መንገድ እንዲሠራ ይዞታቸውን በነጻ የሰጡትን እግዚአብሔር በሰማያዊ ቤት በክብር እንደሚጠበቃቸው ቅዱስ መጽሐፍን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።
በዚህም ደብሩን ከሚመሩት አስተዳዳሪ ሰበካ ጉባኤ ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴና ማኅበረ ካህናትና በጎ አድራጊ ምእመናን ከፍተኛ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ በረከትና አባታዊ መልእክት በደብሩ የተሠሩትን ሥራዎች በእጅጉ አድንቀው በተለይ ዛሬ የተመረቀው አዲስ መንገድና ድልድይ ተግባብቶና ተስማምቶ የመሥራት ውጤት ነው ብለዋል። በዚህም ለደከሙ ለታዘዙ ለመሩ ሁሉም ምስጋና ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ቀጥለው ከንቱ ንግግርና ወሬ ለተቋም እንደማይጠቅም ለክርስትና ሕይወትም እንደማይበጅ ጥቅምት 8 ቀን ዕረፍቱ የሚታሰበውን የአባ አጋቶን ታሪክን በማንሳት ያስታወሱ ሲሆን ሥራዎች ሁሉ በዕቅድ መመሥረት እንዳለባቸውና ከወሬ ይልቅ በተግባር ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አያይዘውም ለዓመታት የግንባታ ሂደቱ የዘገየውን የደብሩን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በፍጥነትና በርብር በመሥራት በዚህ ሁለት ወራት ውስጥ እስከ ትንሣኤ ድረስ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚታይበት እምነታቸውን ገልጸዋል።