የ ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም የቃና ዘገሊላና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብረው መዋላቸውን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከጥር ፲ እስከ ፲፪ ቀን የሚከበሩት የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት ዘንድሮም በመላው ኢትዮጵያ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት እጅግ ሰላማዊ በሆነና በተዋበ መልኩ ተከብረው ውለዋል።
እነዚህ በዓላት በቤተክርስቲያናችን እጅጉን መንፈሳዊ በዓላት ከመሆናቸው በተጨማሪ በሰላም፣በስምምነት፣በአንድነትና በመከባበር መገለጫነት የሚታወቁ በዓላት በመሆናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምትገኝባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብረው መዋል ይችሉ ዘንድ መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት፣ምዕመናን፣ምዕመናትና ወጣት ልጆቻችን ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። ይህም በመሆኑ በልዑል እግዚአብሔር ረድኤትና በረከት ስኬታማ በዓል ለማክበር ችለናል።
ለዚህም ልጆቻችን በዓሉ የቤተክርስቲያያችንን ክብር በሚመጥን መልኩ ተከብሮ እንዲውል በማድረግ ረገድ ያሳያችሁት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጨዋነትን የተላበሰ የበዓል አከባበር ሥርዓት የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።በዚህም ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከፍተኛ ወጪ በማድረግ የክብር እንግዶች በዓሉን ያከበሩበትን ስቴጅና ሳውንድ ሲስተም ከነ ሙሉ ግብዓቶቻቸው በማቅረብ ለበዓላችን ድምቀትና ማማር ትልቁን አስተዋጽኦ በማበርከት የሚያስመሰግን ተግባር ፈጽመዋል፤
ለዚህም በተለይ ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ላደረጉልን ከፍተኛ ድጋፍ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ስታቀርብ እግዚአብሔር አምላክ ረጅም እድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር እንዲሰጣቸው ከመለመን ጋር ነው።
በተለይም በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሌት ከቀን ስትደክሙ የሰነበታችሁ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት፣የጸጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አባላት፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ አተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አመራሮች በዓሉ በሰላም ተከብሮ መዋል እንዲችል ደከመን ሰለቸን ሳትሉ ላሳያችሁት ትጋት ቅድስት ኦሮቶዶሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ምስጋናዋን እያቀረበች እግዚአብሔር አምላክ ሥራችሁን ሁሉ እንዲባርክና የዘወትር ጥበቃው እንዳይለያችሁ አጥብቃ እንደምትጸልይላችሁ ትገልጻለች።
ከበዓሉ በፊት በዓሉን በተመለከተ የቤተክርስቲያናችንን መልዕክት በማስተላለፍ፣በበዓሉ ወቅትም የበዓል አከባበር ሥርዓቱን ለመላው ዓለም በቀጥታ ሥርጭትና በዜና በልዩልዩ ቋንቋዎች በመዘገብ በዓላችንን በከፍተኛ ሁኔታ ስታስተዋውቁ ለሰነበታችሁ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞችም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን እያቀረበች ሥራችሁ ሁሉ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቷን ትገልጻለች።
በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ወጣት ልጆቻችን በዓሉ በድምቀት እንዲከበር መንፈሳዊ መልዕክቶች በአግባቡና በተለያዩ ሥነ ጥበባዊ መንገዶች እንዲተላለፉ፣በተለይም በዓላቶቻችን ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነትን በተላበሱ መልኩ ተከብረው እንዲውሉ ቤተክርቲያን ባስተማረቻችሁ የመተሳሰብ፣
የመደጋገፍና የመከባበር ሥርዓት መሰረት የሚጠበቅባችሁን ሃይማኖታዊ ግዴታ በሚገባ በመወጣት ያሳያችሁት መንፈሳዊ ትጋት ለቤተክርስቲያናችሁ ኩራትን ያጎናጸፋት በመሆኑ
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ታቀርባለች።
በመጨረሻም በከተራ በዓል ወቅት በሸገር ሲቲ አካባቢ በአገልግሎት ላይ የነበሩ አራት ወጣት ልጆቻችን በደረሰባቸው የኤሌክትሪክ አደጋ ሕይወታቸውን በማጣታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተሰማትን ጥልቅ ኃዘን እየገለጸች ልዑል እግዚአብሔር ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥልን፣የሟች ልጆቻችንን ነፍስ ደግሞ በደጋጎቹ አባቶቻችን ጎን እንዲያሳርፍልን ዘወትር በጸሎቷ የምትማጸን መሆኗን ትገልጻለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ጥር ፲፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
አዲስአበባ ኢትዮጵያ
