የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ለአራተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ፳፮ (26) ደቀ መዛሙርት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በተገኙበት አስመረቀ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት የሚገኘው የሆሣዕና ካህናት ማሰልጠኛ ተቋም በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ፣ ሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ከተለያዩ ወረዳ ቤተ ክህነቶች የተወጣጡ 26 ደቀ መዛሙርትን ለሦስት ወራት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች ዙሪያ ሥልጠና ሲወስዱ ለቆዩት ሠልጣኞች የምርቃት መርሐ ግብር በሀገረ ስብከቱ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ አከናውኗል።የሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት የቤተክርስቲያንን ቀኖናዋን፤ ዶግማዋን ፤ሳይፋለስ፤ ሳይከለስ፤ ቀጥተኛውን የቤተክርስቲያንን ትምህርት እንዲያስተምሩና በሕይወታቸው ወንጌልን መስበክ እንዳለባቸው፤የቤተክርስቲያን ኃላፊነትም ጭምር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በብፁዕነታቸው ሥልጠናውን ለተከታተሉ ደቀመዛሙርት የሽልማት እና የምስክር ወረቀት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በዕለቱም በሆሣዕና ማሕበረ ቅዱሳን ሆሣዕና ማዕከል በሀዲይሳ ቋንቋቸው በነገረ ድኅነት የተጻፈዉ መጽሐፍ ተመርቋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ለተመራቂ ልጆቻቸዉ ባስተላልፉት አባታዊ መልዕክት “”ሤመክሙ እግዚአብሔር ጳጳሳተ፥ ቀሳውስተ፥ ወዲያቆናተ፤ ከመ ትርአዩ ቤተክርስቲያኑ እንተ አጥረያ በደሙ፤ ወአተባ በዕፀ መስቀሉ” የዛሬ ተመራቂዎቹ የነገዋ ቤተክርስቲያን ተረካቢዎች መሆናቸዉን ገልጸዉ፣የተሰጣቸዉን አደራ በመጠበቅ የገጠሪቷን ቤተክርስቲያን እንዲያገለግሉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዉ በክቡር በብፁዕነታቸዉ ጸሎት የምረቃ መርሐግብሩ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የሀገረስብከቱ የየመምሪያው ክፍል ኃላፊዎች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች ፣ ሊቃውነት ፣ የጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፣ የተመራቂ ደቀመዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
