የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር አካሄደ።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት በየዓመቱ በበዓለ ልደት፣ በበዓለ ፋሲካና በዘመን መለወጫ በዓል ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር እንደሚያከናውን የሚታወቅ ነው።በዚሁ መሠረት የ2018ዓ.ም. የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል አስመልክቶ በዛሬው እለት የእንኳን አደረሰዎ መርሐግብር የተካሄደ ሲሆን በመርሐግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስአበባ፣ የሐድያና ስልጤ አልጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ረ/ ፕ ግርማ ባቱ (ቀሲስ) የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ሓላፊዎችና መላው ሠራተኞች የአአዲስአበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ም/ሊቃነ መናብርት ጸሐፊዎች ልዩ ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሥራ ኃላፊዎች የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ፡ ሓላፊዎችና ደቀ መዛሙርት የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ምእመናንና ምእመናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተገኝተዋል፡፡
መርሐግብሩ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ መሪነት በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ካህናትና ዲያቆናት ጸሎተ ወንጌል አድራሽነት በጸሎት ተከፍቶ የተጀመረ ሲሆን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ደቀመዛሙርት ያሬዳዊ ዜማ በማቅረብ ቅዱስነታቸውን እንኳን አደረሰዎ ብለዋል።
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ተወካዮች፣ በጽሑፍ የእንኳን አደረሰዎ የደስታ መግለጫ ያቀረቡ ሲሆን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማእከላዊ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በወረብ የጋሞኛ ቋንቋ ዘማርያን በመዝሙር እንዲሁም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቅኔ እንኳን አደረሰዎ ብለዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለቅዱስነታቸው የእንኳን አደረሰዎ መልእክት ሲያስተላልፉ በዓለ ልደት የሰው ልጆችን ለማዳን ሰው የሆነ የአምላካችን ቸርነት፣ የፍቅሩ መጠንና የማዳኑ ሥራ በተለየ አድናቆት የሚታሰብበትና በተደረገልን ፈንታ ከእኛ የሚጠበቀውን ሕይወት የሚነገርበት ታላቅ በዓል መሆኑን በማውሳት “እስመ ሶበ ርኢነ ዘመደ ሥጋነ ንሴብሖ ለመለኮተ ወልድ በሒሩቱ ለአብ (በሥጋ ዘመዳችን ሆኖ ባየነው ጊዜ በአብ ቸርነት የወልድን ጌትነት እናመሰግነዋለን) በማለት የተናገረውን የሊቁን ቃል በማንሳት የጥበብ ሰዎች ለተወለደው ሕጻኑ ንጉሥ ወርቅ ዕጣንና ከርቤ ስጦታ ያቀረቡበትን ነገር በማሰብ ከቁስ በላይ የሆነውን ፍቅር፣ ቅን ሐሳብና መልካም ምኞት ለቤተ ክርስቲያን መስጠትም የበዓሉ ልዩ ገጽታ መሆኑን በመግለጽ ቤክርስቲያናችን በቅርቡ ለመከናወን የታቀዱ የልማት ሥራዎች የሚጠይቁት መዋዕለ ንዋይ፣ ሐሳብ ጊዜና ጉልበት እጅግ ብዙ መሆኑን በመረዳት በልማታዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ በሚቻለው ሁሉ መተባበር፣ ሓላፊነትንም መወጣት ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ሐመረ ኖሕ ቅዱስ ገብርኤል ሥራ አመራር ኮሌጅ የበላይ ኀላፊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሲሰጡ በልደቱ ሰላም ፣ እርቅ፣ አንድነትና መተባበር መወለዳቸውን በማንሳት ሁሉም ሰው ለዚህ ልዩ ጸጋ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ እንዲያከብር አሳስበው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
