የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ

ከሰሞኑ በአገልጋይ ሄኖክ (በጂፕኤስ) ቴሌቬዠን የተላለፈው መልዕክት የተከበረውን የሰላሌን ማህበረሰብ የማይመጥን እና አጠቃላይ የማህበረሰባችንን መልካም ባህሎችና እሴቶቻችንን የማይወክል መልዕክት በመሆኑ ጉባኤያችን ይህንን ተግባር በፅኑ ያወግዛል።
እንዲህ አይነት ተግባራት መጠኑና ይዘቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም የእምነት ተቋማት አከባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።
እንደዚህ አይነት በሃይማኖት ተቋማት ስር ተጠልለው የጥላቻ ንግግሮችንና፣ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦች የጥላቻ ንግግሮችን በሶሻል ሚዲያ ማስተላለፍ ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል በተለይ ግጭት ቀስቃሽ ፀብ ጫሪ፣ መልዕከቶች፣ የተሳሳቱ መረጃዎች ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ማንቋሸሽ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ ልማድ እየሆነ መጥቷል።
በተለይ እንዲህ አይነት ግለሰቦች ጀግና ለመባል ታዋቂ ለመሆን አልፎም መሰሎቻቸው ስለሚያጨብጭቡላቸውና አድናቆት ስለምሰጡአቸው በሶሻል ሚዲያ ተከታይ ለማፍራት እና በንዋይ ፍቅር ተጠምደው አልፎም ራሳቸውን የሁሉም ነገር አድራጊ እና ፈጣሪ በማስመሰል እያደረጉት ያለው እኩይ ተግባር ሀይ ካልተባለ እና ስርዓት እንዲይዝ ካልተደረገ ይዞ የሚመጣው ችግር ቀላል አይሆንም።
በተለይ እንደነዚህ አይነት ግለሰቦች የትኛውንም የእምነት ተቋማት የማይወክሉ እና የተቋማቱ አቋም አለመሆናቸው ቢታወቅም ነገር ግን የእምነት ተቋማቱን ጥላ ስር ተደብቀው የሚያስተላልፉ በመሆናቸው እንደቀላል የሚታይ ግን አይደለም።
በሃይማኖቶች መካከል፣ እንዲሁም በማህበረሰባችን ዘንድ ጥላቻ እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ የማህበረሰባችንን አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚጎዱ በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማት በግልጽ እንደነዚህ አይነት ግለሰቦችን ቀድመው ሊመክሩ፣ ሊገስፁ እና ልያወግዙ ይገባል።
በተለይ የሃይማኖት መምህራን ሰባኪያን ፈጣሪ ያስተማረን ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብዓነትን እንዲናሳይ ሰውን እንድናከብር ፣ ርኅራኄን ፣ፍቅርን ትህትናን ይቅርታን ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲናደርግ እንዲሁም ሃይማኖትን፣ ብሔርን፣ ማህበራዊ መሠረትን ፣ ሳንለይ ለሰው ሁሉ ፍቅርን እንዲናሳይ እንጂ ፀብና ጥላቻ ለመዝራት አልተጠራንም።
ይህን በመገንዘብ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በመምህራንና በሰባኪያን የሚተላለፉ ስብከቶችና ትምህርቶች የየእምነት ተቋማቱን አስተምህሮን መሠረት ባደረገ እሴቱን ጠብቆ እንዲሰበክ የማድረግ ስህተት ሲኖር የማስተካከል ፣ የማረም ሃላፊነት እንዳለባችሁ እንገነዘባለን።
የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ከመፈጠራቸውም በፊት የማስተማር የመምከር ከተፈጠረ በኃላ ደግሞ ፈጥኖ የሚታዩ የአስተምህሮ ዕፀፆችን የማረም ሃላፊነትን በተገቢ ሁኔታ እንዲትወጡ አደራ ማለት እንወዳለን።
የመንፈሳዊ ሚዲያ ባለቤቶችና ባለሙያዎች ሀገራችን የብዝሀ ሃይማኖት ፣ የብዝሀ ቋንቋ እና ብዙ መልካም ባህሎች ያላት ሀገር ናት ይህ ብዝሀነት በአግባቡ ከተጠቀምንበት መርገም ሳይሆን በረከት እና ትልቅ ዕድልም ነው። የሚዲያ ባለሙያዎች የተቋሞቻችሁን ዓላማ ለማሳካት በሚታደርጉት ጥረት ሁሉ ሃይማኖታዊ እሴቶቻችሁንና ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዝሀነትን ባከበረ መንገድ እንዲሁም የሀገርቱን የብሮድካስት ሕግ እና የተቋሙን የሥነምግባር መመሪያ በማክበር ኃላፊነታቸውን እንዲትወጡ እናሳስባለን።
በተለይ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ሚዲያዎች የስነ ምግባርና የሞራል መሠረት ሊሆኑ ይገባል እንጂ በማህበሰባችን ዘንድ ግጭት ቀስቃሽ ፣ፀብ ጫሪ ሐሰተኛ መረጃ ሲተላለፍ በዝምታ ልታዩ አይገባም በምትሠሩት ሙያ ተጠያቂነት እንዳለ ጭምር ልናስታውሉ ይገባል። ከሃይማኖት ከመልካም ባህሎቻችንና ከእሴቶቻችን ወጣ ያሉ ነገሮችን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግም ይሁን ሲደረግ በቸልተኝነት ዝም ብሎ መመልከት ከተጠያቂነት አያድነንም ሰለዚህ ለሙያው እንዲሁም ለተቋቋማችሁበት ዓላማ በታማኝነት እንዲትሰሩ እንመክራችኋለን።
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በስራችሁ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎቻችሁ የተቋቋሙበትን ዓላማ በትክክል እየፈፀሙ መሆናቸውን በየጊዜው ማየት መፈተሽ ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ይረዳል አልፎ ስህተቶች ሲፈጠሩ የእርምት እርምጃ በወቅቱ መወሰድ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።
መንግስት ለሠላም እና ለልማት እንዲሁም ብዝሃነት ባከበረ መንገድ የህዝባችን አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን እንዲጎለብት እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ጉባኤያችን በእጅጉ በአድናቆት የሚመለከተው ጉዳይ ነው።
በተለይ ከህዝባችን እምነት፣መልካም ባህልና እሴቶቻችን ወጣ ያሉ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት አጽንኦት በመስጠት ህግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት ሳናመሰግን አናልፍም።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭት ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮችን በመናገርና መልዕክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ በማስተላለፍ ፣ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ብሔርን ከብሔር ጋር ለማጋጨት ፣ የሃይማኖታዊ ምልክቶችን በማነወር በሃይማኖቶች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር እና ለዘመናት የቆዬውን የህዝባችንን የአብሮነት እሴት ለመሽርሽር ሆን ብለው የሚሰሩ አንዳንድ ግለሰቦችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
መንግስት ከዚህ በፊት በሃይማኖቶች መካከል ጠብ ለመጫር የሞከሩ ግለሰቦች ላይ የህግ ተጠያቂነት ለማስፈን ሲያደርግ እንደነበረ ሁሉ ከሃይማኖት ከመልካም ባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ወጣ ያሉ መልዕክት በሚያስተላልፉ የህዝባችንን አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲሸረሸር ሆን ብለው በሚሰሩ ግለሰቦች ላይ የህግ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ሚናውን እንዲወጣ እናሳስባለን።
በመጨረሻም ጉባኤያችን እንደወትሮው ሁሉ የከተማችን ብሎም የሀገራችን ሠላም፣ልማት የህዝባችን ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲጎለብት በሃይማኖቶች መካከል ዘመናትን የተሻገረው የመከባበርና አብሮነት እሴት ይበልጡን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደከተማችንም ይሁን እንደሀገራችን የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የሠላምና የልማት ስራዎች እውን እንዲሆኑ ጉባኤያችን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዘውትር የሚተጋ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን።
አዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ