ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት ለ፺፭(95) ደቀ መዛሙርት የዲቁና ማዕረገ ክህነት ሰጡ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ለ፺፭ ደቀ መዛሙርት የዲቁና ማዕረገ ክህነት ሰጡ።ከብፁዕነታቸው ጋር መልአከ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ፀሐፊ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የቂርቆስ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ገነት ዘማርያም ሙጬ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ አስተዳዳሪ፣ ሊቃውንትና ማዕረጉን የሚቀበሉ ደቀ መዛሙርት ተገኝተዋል።
ማዕረገ ዲቁና የተቀበሉት አገልጋዮች ከተለያዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ መምህራን እየተማሩ የቆዩ መሆኑቸው የተገለጸ ሲሆን ማዕረገ ክህነት ሊቀበሉ ሲመጡም በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ መመሪያ ሰጭነት በየአጥቢያው ባሉ መምህራኖቻቸውና በሀገረ ስብከት ደረጃ ተፈትነው ያለፉ ናቸውም ተብሏል።
ይሁንን እንጂ ምዘናውን የሚሰጡት መምህራና የሥራ ሐላፊዎች በትምህርታቸው ብቁነት እርግጠኛ ያልሆኑባቸውን 5 ዲያቆናት ወደ ብፁዕነታቸው ያቀረቡ ሲሆን ብፁዕነታቸውም የቅስና ሥልጣነ ክህነት ሊቀ በሉ የመጡትን 5 ዲያቆናት እንደገና ምዘናውን በመስጠት ማለፍ ስላልቻሉ በሌላ ጊዜ አጥንተውና ተዘጋጅተው እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
የዲቁና ማዕረገ ክህነት ከተቀበሉ መካከል የ13 ዓመቱ ሕጻን የአብነቱንና የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በተለይም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በአማርኛ በቃሉ በማጥናት የተወሰኑትን በብፁዕነታቸው አቅርቧል።
በተግባሮም ብፁዕነታቸውን ጨምሮ በቦታው የተገኙት ሁሉ አድናቆታቸውን በመስጠት ለቁምነገር ያብቃው በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፯:፪፻፵፩ “ዲያቆኑን በምትሾምበት ጊዜ በእርሱ ላይ እጂህን አስቀምጥና ጸለይ” ቀጥሎም “ኢጲስ ቆጶሱ ብቻ እጁን ይጫንበት” እንዲል ብፁዕነታቸው 95ቱን ደቀ መዛሙርት በአንብሮተ ዕድ የዲቁና ክህነት ማዕረግ የሰጡ ሲሆን እግዚአብሔርን በመፍራትና በማስቀደም እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
አክለውም ስለክህነት ክቡርነትና የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥንቁቅነት ያስታወሱ ሲሆን እምነታቸው ጠብቀው በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን እንዲከናውኑ በአጽንኦት መክረዋል።
በመጨረሻም የዲቁና ማዕረገ ክህነት የተቀበሉት ሁሉም ደቀ መዛሙርት ቅዱስ ሥጋና ደሙ እንዲቀበሉ ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን ሥርዐቱ በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።
