መምሪያው በ25 አህጉረ ስብከት ላይ የቅዱስ ወንጌል ስምሪት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ገለጸ
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በ25 አህጉረ ስብከት ላይ የቅዱስ ወንጌል ስምሪት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ገለጸ።በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ ፲/፳፻፲፰ ዓ/ም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከአዲስ አበባና ከሸገር አህጉረ ስብከት የተውጣጡ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሥራ ሐላፊዎች ጋር ወይይት አድርገዋል።
በምክክሩ ላይ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ሽፈራው እንደሻው የመምሪያው ዋና ጸሐፊ የአዲስ አበባና የሸገርና አህጉረ ስብከት እንዲሁም የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሐላፊዎችና የመምሪያው የሥራ ሐላፊዎች ተግኝተዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እንዲጠናከር በተለየ መንገድ መምሪያ ከተሰጠበት ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሥራዎችን እየተሠሩ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን በተለይም የቅዱስ ወንጌል ተልእኮን የጋራ አድርጎ ከመሥራት አኳያ ስልጠናና ምክክር እንዲሁም ከፍተኛ የግብረ መልስ ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከአክለውም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወዲህ ሁሉም የገዳማትና አድባራት አገልጋዮች ከወር ደሞዛቸው ለቅዱስ ወንጌል አገልግሎት 1 ፐርሰንት ተጠናክሮ እየተከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመምሪያው የመተዳደሪያ ደንብ፣ የአገልጋዮች ሥነምግባር ደንብ በበላይ ሐላፊ ለማጸደቅ እንዲሁም የተደራጀ ሚዲያ እንዲኖር ጠንካራ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መምሪያው በተለይም በአዲስ አበባና በሸገር አህጉረ ስብከት የሚገኙ መደበኛና በትሩፋት የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል ባሳተፈ መልኩ በመላ ኢትዮጵያ በተመረጡ 25 አህጉረ ስብከት የቅዱስ ወንጌል ስምሪት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ተናግረዋል።
የመምሪያው ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሐዲስ ሽፈራው እንደሻው የቤተ ክርስቲያንን ቀዳሚ ተልእኮ የተሸከመው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ራሱን ከቻለ ወዲህ በተለይም መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ከተመደቡ ጀምሮ ከፍተኛ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አክለውም ሥራዎች በዕቅድና ተልእኮን ሁነኛ መሠረት በማድረግ እየተሠሩ እንደሆነም የገለጹ ሲሆን በተለይም ቢሮ በማድራጀት፣ በዲጅታል ሚዲያ እንዲሁም የተቋማት ግንኙነት ላይ ተኩረት በማድረግ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በመቀጠልም በሁለቱ አህጉረ ስብከት መካከል ተቀራርቦና ተናቦ የመሥራት ሁኔታን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በተለይም በቅዱስ ወንጌል ሥምሪት፣ በሥልጠናና የጋራ ተልእኮ ላይ በተኩረት እንደሚሠሩም የሚበረታታ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሸገር ሀገረ ስብከት በአማርኛ እና በኦሮምኛው ቅዱስ ወንጌልን ከማድረሱ በላይ በጋሞኛ ቋንቋን እየተሰበከ እንደሚገኝም የውይይት ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ መምሪያው በዲጅታል ሚዲያ ዘርፍም ራሱን በቻለ ሁኔታ ማጠናከር እንዲሁም የቅዱስ ወንጌልን ተዳርሶውም በኅዘን ቤት፣በእስር ቤት እና በሆስፒታል እየተዘዋወሩ መስበክ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የክርስቶስን ሕያው ቅዱስ ወንጌልን ከኢትዮጵያ ውጭ በአፍሪካም መስበክ የዘለዓለም አደራን መወጣት ጠንከር ያሉ ሥራው ቢሠሩ የሚሉ ሐሳቦችም ቀርበዋል።
በአጠቃላይ ሰባክያኑ እንዳሉት ወንጌል ኑሯችንና መኖሪያች ነውና ከትናንቱ በበለጠ መሥራት አለብን ብለዋል።
የመምሪያው ሐላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድና የመምሪያ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሐዲስ ሽፈራው በተሳታፊዎቹ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
መምሪያውን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመምለስ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ድርሻ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለይም የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ስብከተ ወንጌል ክፍል የመምሪያውን 1 ፐርሰንት በማስከፈልና ለአዲሱ ትግበራ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን በማስታወስ በእጅጉ አመስግነዋል።
አያይዘውም በቀጣይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ትኩረት አድርገው መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ዘመነ አስተርእዮን ለቅዱስ ወንጌል አገልገሎት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመሆኑን በዓላቱንና ዐውደ ምሕረቱን በጭንቀት ውስጥ ላሉ፣ በመከራ ለተያዙ፣ ትከሻቸው ለዛለባቸው፣ በሰው ተከበው ሰው የለኝም ለሚሉ፣ ደጃፋቸው ላይ ደስታ ለራቃቸው፣ ሕይወታቸው አድራሻ የተጠፋባቸውን ሰዎች መሠረት በማድረግ በክርስቶስ ሕያው ቅዱስ ወንጌል ማጽናናትና የማይነጠቅ ተሰፋ ክርስቶስ የማይሰለች አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በእምነት ማስተማር አለብን ብለዋል።
በዚህም የሚመለከታቸው የገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል አገልጋዮችን በመሰብሰብ ውይይትና ምክክር እንዲደረግ መልአከ ሰላም ዳዊት አሳስበዋል።
