በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የተመራ ልኡክ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የታሪክ አሻራ ባለበት በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረገ

በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሣዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የተመራ ልኡክ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የታሪክ አሻራ ባለበት በወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረገ።
በ14ኛው መቶ ክፍ ዘመን እንደተመሠረተ የሚነገርለት የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የታሪካዊ ቅርሶችና የአያሌ ንዋያተ-ቅዱሳት ባለቤት ነው። ከነዚህም መካከል አፄ ዘርዓያዕቆብ ለቤተ ክርስቲያኑ ያበረከቱት ገድለ-ቂርቆስ፣ አፄ ፋሲለደስ ያበረከቱት የብረት መረዋ/ደወል/፣ ዜና ፋሲል የተሰኘ መጽሐፍት ይጠቀሳሉ።
የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የበገዳሙላይ የታሪክ አሻራቸው የሚታወስ ሲሆን ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ የሣር ክዳን የነበረውን ቤተክርስቲያን የቆርቆሮ ክዳን አልብሰው ማሳነጻቸው ታሪክ ይመሰክራል ።
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው ታሪካዊው የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የዘመናት መልኩን ታሪኩን መሠረት በማድረግ በልዩ የሕንጻ ጥበብ ቤተክርስቲያኑ እየተሠራ ይገኛል።
ይህንን አስመልክቶም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራ የልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት በወንጪ ይፋዊ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቅስ የአዲስአበባና የሀድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ፣ አሪ ዞኖች ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣
፣ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የከምባታ ሀላባና ጠምባሮ አህጉረ ስብከት ጳጳስና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደገለጹት ገዳሙ ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከያወኑ መሆኑን ገልጸው ከሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ በተጨማሪ የአብነት ትምህርት ቤት፣ሰንበት ትምህርት ቤት፣ሰንበቴ ቤት፣ሙዚየምና ወደ ገዳሙ የሚያስገባ ወደብ የሚገነባ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።አያይዘውም ቦታው የቱሪስት ፍሰት የሚበዛበት መሆኑን ታሳቢ በማድረግም ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች እንደሚከናወኑ የጠቀሱት ሙሐዘ ጥበባት አጠቃላይ የግግባታ ሥራው በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
የገዳሙ አጠቃላይ የግንባታ ሥራን በተመለከተም በባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል።የቤተክርስቲያኑ ግንባታ ሥራ ኃይማኖትን፣ታሪክንና ባህልን መሰረት ያደረገ እንደሆነም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተውጣጥተው የተገኙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችም ለዚህ የተቀደሰ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በዚሁ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልዕክት የወንጪ ቂርቆስ ቤተክርስቲያንን ለማሰራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መሆናቸውን ገልጸው ሀይማኖት፣ታሪክና ባህልን አስተሳስሮ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በተግባር የሚሰብከውን ፕሮጀክት በማስተባበርና በመምራት ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።አያይዘውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወንጪን በመሳሰሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥንታዊያን ገዳማትና አድባራት ታድሰውና ታንጸው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በማድረግ በታሪክ ውስጥ የሚዘከር ሥራ እየሰሩ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በጸሎቷ ታስባቸዋለች፣ ምስጋናዋንም ታቀርባለች ብለዋል።