የአትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች መጻሕፍትን አበረከተ

የአትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች መጻሕፍትን አበረከተ ።
በመርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመምሪያው የበላይ ሊቀ ጳጳስ ሊቀ ኅሩያን ይልማ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የመምሪያው ሐላፊ እንዲሁም የየተቋማቱ የሥራ ሐላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን ይልማ ጌታሁን ማኆሩ ለመምሪያው ያበተከታቸው መጻሕፍት በ21 ዓይነት እና በ19 ቋንቋዎች እንዲሁም በድምጽ የተዘጋጁ መጻሕፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዋና ጸሐፊው ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር በተለይም ዋና ተልእኮዋን በቀጥታ ከሚያስፈጽመው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ጋር በስልጠናና በወንጌል ተደራሽነት ዙሪያ ላይ በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያደረገውን የመጽሐፍት ልገሰ በእጅጉ አመስግነዋል።
ለዚህ መልካም ተግባር ምክንያት የሆኑትን መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድን ያበረታቱ ሲሆን ከተመደቡ ጀምሮ የሚያስመስገን ሥራዎችን እየተሠሩ በመሆኑም ሊደነቁ ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው በቋንቋ መስበክ የቤተ ክርስቲያናችን ሁነኛ መንገዷ እንደሆነ የበዓለ ሃምሳን ታሪክ አስታውሰው ያብራሩ ሲሆን አጠንክራ ልትሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነውም ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ያነበቡ በተግባርም በሕይወታቸው የገለጡ አባቶቻችን ከሰው አልፈው ከምድር አራዊት ጋር ተስማምተው የኖሩ በሕይወታችን ያላመዱ ሲሆኑ በዘመናችን ግን ከገዛ ወንድሙና እኅቱ ጋር መግባትና አብሮ በሰላም መኖር አልቻለም ለዚህም በቅድሚያ መጽሐፍቅዱስን በማንበብና በሕይወት በመኖር ራሳችንን አድነን ሌሎችን ለማትረፍና ለማቅናት የሰላም ወንጌልን በሕይወት መስበክ ይገባል ብለዋል።
ያነበበና የኖረ ይስበክ የሚሉት ብፁዕነታቸው እንደ ነቢዩ ሙሴ ጸጋንና የተሰጠን ስጦታ አውቆ ተናጋሪው ሰሚ፤ ሰሚው ተናጋሪ በመሆኑ ጸጋን ባለማወቅ የመደባለቅ ስብራት መጠገን አለበት። ይህም የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ በአግባቡ እንዳይፈጸም ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነም ጠቁመዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ በበኩላቸው መምሪያ እያከናወናቸው የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናዊ ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ ተጠናክረው እየቀጠሉ መሆናቸውን ያስታወሱ ሲሆን በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያበረከተልን መጻሕፍት የመምሪያውን ቤተ መጻሕፍት ከማጠናከሩ በላይ ተቋማቱ በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው የትብብር ሥራዎች ድልድይ እንደሚሆን ገልጸዋል።
አክለውም የመምሪያ ሠራተኛ ተናቦና ተግባብቶ በሁነኛ የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ በአንድነት እየሠራ መሆኑ ገልጸው በተለይም በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በስልጠናና በወንጌል ተደራሽነት ላይ በቅርብት ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።