“ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና ተሰጠ
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በ፳፻፲፷ ዓ.ም ትኩረት በመስጠት እሠራባቸዋለሁ ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የቴክኖሎጂ ልማት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ሐሳብ በማገዝ ረገድ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የመጀመሪያ የሆነውንና “ቴክኖሊጂ ለሁሉን አቀፍ የቤተክርስቲያን አገልግሎት” በሚል ርእስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን አስፈላጊነትና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ልምድና ተሞክሮ ያካተተ ሥልጠና ነው የተሰጠው።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያውን ሥልጠና የሰጡት ዶክተር አዲስ ዓለም ገንታ “ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ ለቤተክርስቲያን ዕድገት” የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ሥልጠና በረዳት ፕሮፌሰር መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ “ዘመናዊ የመረጃና የሥራ ትስስር ቴክኖሎጂን መጠቀም ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ተልዕኮና ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር” በሚል አቅርበዋል፡፡
ዶክተር አዲስዓለም ገንታ የሥልጠናውን ዓላማ እንደገለጹት የቤተክርስቲያን መሪዎችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዙሪያ ዕውቀት ማስጨበጥ፣ የአይሲቲን ጠቀሜታ ማስገንዘብ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ግልጸኝነት፣ ውጤታማነትን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት የሚጨምር አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል እና በመጨረሻም የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶኮስ ቤተክርስቲያን ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ ከእኛስ ምን ይጠበቃል? በሚል ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልም በውጩ ዓለማት ተሞክሮ ላይ በማተኮር ዘመናዊ የመረጃና የሥራ ትስስር ቴክኖሎጂን መጠቀም ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ተልዕኮና ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም እኛ ልንማርባቸው የሚገቡን እና እነሱ የተጠቀሟቸው ዘርፎችንም አብራርተዋል፡፡ እነዚህም፡- በመንፈሳዊ አገልግሎት የቤተክርስቲያንን ዕሴቶች በመጠበቅና በማስጠበቅ፣ በሁለንተናዊ ትምህርትና ሥልጠና፣ በአስተዳደርና ፋይናንስ፣ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ፣ በሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት፣ በወጣቶች አገልግሎት፣ በመዛግብትና በሰነድ አያያዝ ፣ቅርስና ቱሪዝም፣ መንፈሳዊ ጉዞ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት በተቋማዊ ደኅንነትና ሕልውና ዙሪያ አስረድተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ሁላችንም ወደዚህ ቴክኖሎጂ መግባት ይገባናል ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ይህን ሥልጠና ፈቅደው የመምሪያ ኃላፊዎች ውይይት እንዲያደርጉ ማድረጋቸው በጣም አመሰግናለሁ፤ በአሁኑ ሰዓትም በቤተክህነት በብፁዕነታቸው ብዙ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህን የቀረበውን ሥልጠናም ብፁነታቸው የቤተክርስቲያን ባለሙያ ልጆችን አሰባስበው እንዲተገበር ያደርጉታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስም በሥልጠናው የተሳተፉትንም ሆነ አሠልጣኞችንም አመስግነዋል፡፡ በመጨረሻም “የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር መለወጥ ግድ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ምንም ያጣችው ነገር የለም፤ ትኩረት ስላልተሰጠው ብቻ እንጂ፤ ይህን ወደ መሬት ላይ አውርደን ተግባራዊ እናደርጋለን” በማለት ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ሥልጠናው የቴክኖሎጂን አስፈላጊነት በመረዳት እንዲሁም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበትን ደረጃ እንደተሞክሮ የሚያሳይ ነው፡
