ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ “ቆሞሱን ጳጳስ” በማለት በዐውደ ምሕረት የተናገሩት ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ግርማ ይቅርታ ጠየቁ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ሀብታተ ቤተ ክርስቲያን ከሚባሉት መካከል በዘር የማይሰጥ በብሔር የማይታደል፣ ሥጋዊ ደማዊ በሆነ ድምጽ ብልጫ የማያገኙት፣ ልሁን ስላሉ የማይሆኑት አልፈልግም ስላሉም የማይቀር በመንፈስ ቅዱስ መራጭነት እንደቸርነቱ ለተገባቸው አካላት ብቻ የሚሰጠው “ሀብተ ክህነት” ዋነኛው ነው።
ይህን ሀብተ ክህነት ደግሞ ሐዋርያዊት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ክብረ ክህነትን በቀኖና ጠብቃ፣ ከትውልድ ትውልድ አልፋ እዚህ እንደደረሰች የመጣችበት የጉዞ ታሪክ ይመስክራል።
ሰሞኑን ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ግርማ የፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን “ቆሞሱን ጳጳስ” በማለት በዐውደ ምሕረት የተናገሩት የቀኖና ጥሰት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዳያ ሲመላለስ መክረሙ በዚህም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለምን ዝም አሉ? የሚሉ ሐሳቦች ሲቀርብበት መሰንበቱ የሚታወስ ነው።
በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የሚመራው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባካሄደው መደበኛ የአስተዳዳር ጉባኤ “ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ግርማ ኅዳር ፲፩ /፳፻፲፰ ዓ/ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓል ላይ ትምህርተ ወንጌል ለመስጠት የተጋበዙትን ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱን የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪና የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜና ቅኔ መምህር ከቀኖና ውጭ”ጳጳስ” “ብፁዕ አባታችን ” በማለት መጥራታቸውን በማስረጃ በማረጋገጥ ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክቷል።
በመሆኑን ከላይ በተጠቀው መልኩ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን በጉዳዩ ተጠቃሽ የሆኑትን ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰንና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ግርማ በአካል እንዲቀርቡ አድርጓል።
ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱን የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪን ከቀኖና ውጪ “ጳጳስ” “ብፁዕ አባታችን” በማለት መጥረታቸውንና ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነው ይሁን እንጂ ከተፈጸመው የቀኖና ጥሰት ጀርባ የመድረክ አጠቃቀም ችግር እንጂ ሌላ ተልእኮና ዓላማ እንደሌላቸው ለጉባኤው ገልጸዋል።
አክለውም በተፈጸመው ድርጊት ስህተተኞች መሆናቸውን ጠቅሰው ይቅርታ እንዲረግላቸው በጉባኤው ፊት የጠየቁ ሲሆን በጽሑፍም የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተዋል።
በብፁዕነታቸው የሚመራው የሀገረ ስብከቱ የአስተዳዳር ጉባኤም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ሐዋርያት 20፥28) የሚለው ሐዋርያዊ ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ ብፁዕነታቸው ብሎም ሀገረ ስብከቱ የቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሐላፊነት መወጣት እንደለበት በማመን በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።
በተለይም “ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።”
(1ኛ ቆሮ 14፥40) ብላ የምታስተምር ” ወዲህ ደግሞ “ከተጻፈው አትለፍ”(1ኛ ቆሮ 4፥6) ብላ የምታስጠነቀቅ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን በልኩና በተቀመጠው ሥርዓት መፈጸም እንደሚገባ የዘወትር ትምህርቷ መሆኑን ጉባኤ አስታውሷል።
በተለይም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፱:፪፻፺፪
“#ሁሉም እያንዳንዱ በተሰጠው መዓርግ ይኑር ። ከእናንተ ወገን አንድስ እንኳ ያልተሰጠውን የባልንጀራውን መዓርግ አይቀማ” የሚለው መመሪያ ገዢና ትውፊታዊ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ እውነት መገዛት እንደነበረባቸው በስፋት ተነስቷል።
በመሆኑን ጥፋቱ በቀጥታ ቀኖናን የጣሰ፣ ለሌሎችም በር የሚከፍት ቅዱሱን ዐውደ ምሕረት ከሥርዓት ውጭ ላልተገባ ጉዳይ የመጠቀም የሚሉ ጥፋቶች መፈጸማቸውን ጉባኤው አረጋግጧል።
ይሁንና ከሥርዐት መጽሐፍት መካከል አንዱ በሆነው በመጽሐፍ ዲድስቅልያ “ኤጲስ ቆጶሳት በፍቅርና በቅንነት የሚመለሱትን ንስሐቸውን ይቀበሉ … የእግዚአብሔርን ቸርነት እዩ ፤ ያለ ምሕረት በማክበድና በልብ ተንኮል የሚፈርዱትን አይደለምና ነገር ግን ወደ ንስሐ መመለስን ይችሉ ዘንድ የበደሉትን በበጎ አምልኮ መልሰው ይቀበሏቸው”(ዲድስቅልያ አንቀጽ ፮:፩) የተባለው ትዕዛዝና ወዲህ ደግሞ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ በረጅም ሥራ ጊዜ የሚያውቋቸው አካላት ቀናነታቸውና ለይቅርታ ቅርብ እንደሆኑ የተመሰከረ ሲሆን ያስገቡት ይቅርታ በብፁዕነታቸውና በጉባኤ ተቀባይነት አግኝቷል።
በመሆኑም ሊቀ ኅሩያን ዳዊትና መጋቤ ሐዲስ ቃለ ጽድቅ ቀኖናዊ ጥሰት መፈጸማቸውን በማመናቸውና ከዚያም በአካልና በጽሑፍ ይቅርታ ስለጠየቁ አስተዳዳር ጉባኤው የሚከተለው ውሳኔ አሳልፏል።
፩ኛ. ከብፁዕ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ቀኖና እንዲቀበሉ
፪ኛ.የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው
፫ኛ.በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ በይፋ ቤተ ክርስቲያንና ማኅረ ካህናት እንዲሁም ምእመናን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማለት ውሳኔ አሳልፏል።
አስተዳደር ጉባኤው አያይዞም በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙ ሁሉም የሥራ ሐላፊዎችና አገልጋዮች ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጠብቀውና አስጠብቀው እንዲያገለግሉ ያሳሰበ ሲሆን ይህንን በማይፈጽሙና በማያስፈጽሙ አገልጋዮች ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አስተዳደራዊ ርምጃ በመውሰድ ጭምር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደሚያስጠበቅ በውሳኔው ገልጿል።
