ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በየካ አባዶ አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በየካ አባዶ አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ።
በጉብኝቱ ከብፁዕነታቸውን ጋር መጋቤ አእላፍ ማሙየ ሸዋፈራው የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፣ መጋቤ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ፕሮቶኮልና ልዩ ጸሐፊ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ጸጋየ ወርቁ ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መጋቤ ሃይማኖት አብርሃም ገብረ ሥላሴ የደብሩ ዋና ጸሐፊ፣ የደብሩ ሰብካ ጉባኤ አባላት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸው በደብሩ የተሠሩና እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሚገኘው የካ አባዶ አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ሁሉን አቀፍ የአገልግሎትና የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ጸጋየ ወርቁ ለብፁዕነታቸው ገልጸዋል።
ከነዚህ መካከል የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ በሕጋዊ መልኩ ማስከበር፣ የአጥር ሥራ፣ የመኪና ጥሪጊያ መንገድ ሥራ ፣ የሻማና ጧፍ ማምረቻ እንዲሁም የዱቄት ማምረቻና የእንጀራና ዳቦ መጋገሪያ የልማት ሥራዎች እንደሚገኙም አስተዳዳሪው አስረድተዋል።
በተጨማሪም በአንዲት በጎ አድሪጊ ክርስቲያን ሙሉ ወጪ ተሸፍኖ እየተሠራ የሚገኝ የጸበል ክፍሎችና ዘመናዊ የአስተዳዳር ቢሮዎችን የያዘ ሕንጻ በፍጥነት እየተገነባ እንደሚገኝም ተገልጿል።
መልአከ ምሕረት ጸጋየ ወርቁ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሚመራው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዘመኑን የዋጀ አሠራርን ከማጠናከር በዘለለ በበርካታ ዘመናት ከመደበኛ አገልገልት ውጭ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በተለያዩ የሥራ ቦታዎች መመደቡ እንዲሁም በእንግልትና በችግር ውስጥ የነበሩ አገልጋዮችን መፍትሔ እየሰጠ ስለሚገኝ በእጅጉ እናደንቃለን ብለዋል።
የደብረ ሰበካ ጉባኤ ምክልት ሊቀ መንበር በኩረ ምእመናን ካሳሁን አበራ ደብሩ በልማቱ እየሠራቸው ከሚገኙ በርካታ ሥራዎች ጎን ለጎን በቅዱስ ወንጌል አገልግሎትም በተጠናከረ መልኩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
አክለውም የአብነት ትምህርት ቤት በማጠናከር ረገድም በጋራ መኖሪያ ቤት ያሳይቀር ከ150 በላይ ሕጻናት እየተማሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በተጨማሪም አክሊለ ኢየሱስ በተባሉ ኦርቶዶክሳዊ በጎ አድራጊ በቅዱስ እግዚአብሔር አብ ስም በደብሩ የሚታነጸ ቤተ ክርስቲያን እንዳለም አስረድተዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ ክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት መልካም የሥራ ክትትል የሚያደርግበት ደብር እንደሆነ አስታውሰው በአፈጻጸሙም የጥሩ የሚባል እንደሆነም ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው “እንደሰማን እንዲሁ አየን” የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ቃል መነሻ አድርገው ቃለ በረከትና የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸው ላይ በደብሩ ተዘዋውረው የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች በእጅጉ የሚያስደንቁ መሆኑቸውን የተናገሩ ሲሆን በዚህ በበጎ አመራር ለመሩ ላስተባበሩ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ጸጋየ ወርቁና የሰበካ ጉባኤ አባላት እንዲሁም በጎ አድራጊ ምዕመናንን ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም በደብሩ የተሠሩት ተመጋጋቢ ሁሉን አቀፍ ልማቶች ” በጌጠኛው ቤትህ ልማት ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ከመፈጸም በዘለለ ለሌሎች አርያአያ የሚሆን እንዲሁም ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የምዕመናንን ትከሻ የማያጎብጥ የሚበረታታ የልማት ሥራ ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ቀጥለውም በደብሩ የልማት ሥራ ውስጥ ፈቃዳቸውን፣ ጉልበታቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን የሰጡ በጎ አድራጊ ምእመናን አመስግነው እግዚአብሔር ብድራት እንደሚከፍል በማይታይ የመስጠት መንገዱ በበረከት፣በጤና፣ በመልካም ሕይወት ይጠብቃቹኋል በማለት አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።
የየካ አባዶ አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተ ከ10 ዓመታት በላይ እንደሆነው የደብሩ መረጃ ያመለክታል።
