ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ቤተክህነት በዋዳ ደብረ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አዲስ ለሚሰራዉ ሕንፃ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ አኖሩ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ እንዲሁም የሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያዊ አገልግሎት በሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ቤተክህነት በዋዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አዲስ ለሚሰራዉ ህንፃ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።
በዕለቱ በደብሩና በባደዋቾና የአጉራባች አድባራት አባቶች ካህናት፣ወንድሞች ዲያቆናት፣ የሺንሺቾ ሕዝበ ክርስቲያን ፣የሀገር ባህል ሽማግሌዎች ፣የመንግስት ባለስልጣናት ፣ምዕመናንና ምዕመናት ፣በተገኙበት ለብፁዕነታቸው ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በዕለቱም ብፁዕነታቸዉ አዲስ ለሚሠራው ህንፃ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ያኖሩ ሲሆን በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፣የዘመናዊ ግብርና ፕሮጀክት ፣ በወረዳ ቤተክህነቱ እንዲሰራ መሰረት ያኖሩ ሲሆን፤የህንጻ ቤተክርስቲያን ሥራ በአጭር ጊዜው እንዲጀመር ብፁዕነታቸዉ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ስራው ሲጀመር እንደሚሰጡ አብስረዋል።
በሀገር ሽማግሌዎች የምርቃትና የእንኳን ደህና መጡልን የደስታ መግለጫ ለብፁዕነታቸዉ የተደረገ ሲሆን በአካባቢዉ ከ50 ዓመት በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በብፁዕ ሊቀጳጳስ በመባረካቸዉ የተሰማቸዉን ደስታ ለሚዲያ ክፍላችን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸዉ ሁላችንም በመደጋገፍ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑን መስራት እንዳለብን ፣ለወረዳ ቤተክህነቱ የስራ ክፍል ኃላፊዎች አባታዊ የስራ መመሪያ ሰጥተዉ ወደ መንበረ ጵጵስናቸዉ ተመልሰዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ ፣መምህር ሞላ ዓለሙ የሀገረ ስብከቱ የትምህርትና ስልጠና ክፍል ኃላፊ፣የምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ብርሃኑ፣ እንዲሁም የደብሩ ካህናትና ዲያቆናት፣ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
ዘገባው የብሕንሳ ሚዲያ ነው።
