ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት በአመካ ወረዳ ቤተ ክህነት በጥንታዊው ቦራራ ደብረ አሚን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ እንዲሁም የሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት በአመካ ወረዳ ቤተክህነት ቦራራ ደብረ አሚን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል።
ቦራራ ደብረ አሚን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በ1907 ዓ/ም የተተከለና በሀገረ ስብከታችን ጥንታዊ አድባራት አንዱ መሆኑ በወረዳ ቤተክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ለብፁዕነታቸው ተገልጿል።
ብፁዕነታቸዉ በደብሩ በማለቅ ላይ ያለውን ህንጻ ቤተክርስቲያን የጎበኙ ሲሆን ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለምዕመናን አገልግሎት እንዲሰጥ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በዕለቱም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ ፣የአመካ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ትግስቱ ሀንዳጎ እንዲሁም የደብሩ ካህናትና ዲያቆናት፣ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።
የሀዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት ብፁዕነታቸው የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ሐምሌ ፱/፳፻፱ ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ አንብሮተ ዕድ ከተሾሙ ጀምሮ በአባትነት የሚያገለግሉበት ሀገረ ስብከት እንደሆነ የሚታወቅ ነው።
