ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር ክቡር ዶክተር እንዳሻው ጣሰዉ ጋር ውይይት አደረጉ
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር ክቡር ዶክተር እንዳሻው ጣሰዉ ጋር በፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት ውይይት አደረጉ።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሀገር ጠቀምና ትውልድ ተኮር ሥራዎች ላይ በሰፊው የምታገለግል እንደመሆኗ በክልሉ የሚከናወኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች የድርሻዋን የምትወጣ ሲሆን በተለይም ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ በሆኑ የልማት ጉዳዮች ላይ በክልሉ ብሎም በሀገራችን ፍጹም ሰላም እንዲኖር በጸሎትና በሚመለከታት ጉዳዮች ዛሬም እንደትንቱ ታላቁን ሚናዋን በማጠናከር ዙሪያ ተወያይተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በዚህ ወር መጨረሻና ሚቀጥሉት ተከታታይ ወራት ለሚከናወኑ ታላላቅ ኩነቶች በብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለቤትነት በሚከናወነው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ ቀዳሚውን ድርሻ በመውሰድ እንግዶችን በመቀበልና በዓላቱ በሰላም ተጀምረው እስኪፈጸሙ በጸሎትና ሕዝብን በማንቃት ለክልላችን እና ለሀገራችን ሰላም ተግቶ ስለመሥራት ተወያይተዋል።
ወደ ፊት በሚኖረው የመንግሥትና የሀገረ ስብከታችን ግንኙነት በየድርሻችን ለሰላም ለልማት እና በተዋረድ እየተጠየቁ ለሚመጡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተነጋግረዋል ሲል ብሕንሳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ዘግቧል።
