ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ። የቅዱስነታቸው መልእክት የሚከተለው ነው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
‹‹ወስሙ ለካልእ ፈለገ ግዮን ወውእቱ ዘየዐውድ ኵሎ ምድረ ኢትዮጵያ፦
“የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል ” (ዘፍ 2+13)
ኢትዮጵያ የሚለው ስም ጽርዓዊ፣ ደኃራዊ ስም ሲሆን ቀደም ሲል የኖኅ የልጅ ልጅ በሆነው በኵሽ ምክንያት የኵሽ ምድር እንዲሁም ምድረ አዜብ፣ ምድረ ሳባ፣ ምድር ኣግዐዚት በመባል ተጠርታለች፡፡ ለዘመናት ኢትዮጵያን ቋሚ አድርገው ካቆዩ ዐምዶች መካከልም ፈለገ ግዮን የተባለው የዓባይ ወንዝ እና ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር- ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› (መዝ. 67÷31) የሚለው የተስፋ ቃል እንደሆነ የታመነ ነው፡፡ በመሆኑም በመግቢያችን ላይ ባነሳነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የኢትዮጵያ ትእምርት ተደርጎ የተጠቀሰው ፈለገ ግዮን በእኛ ዘመን ለሕዝቡ ብርሃን እያበራ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ በማስከተልም የዛሬዋን ቀን በመናፈቅ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ለዚህ ሥራ በማዋጣት ታሪክ በመልካም የሚያስታውሰውን ዋጋ የከፈላችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ልጆቻችንን እንኳን ደስ አላችሁ! ለማለት እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ወደቀጣይ የልማት ሥራ የሚያሸጋግር እንዲሆን፤ ከምንም በላይ _ ሰላም በምድራችን ላይ እንዲስፍን ሕዝባችንም እግዚአብሔር የሰጠው በነፃነት የመኖር መብት ተከብሮለት የልማቱን በረከት መሳተፍ እንዲችል ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም.