በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ የዐዲስ ዓመት የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ያስተላላፉት የእንኳን አደረሰዎ መልእክት

< ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው፡፡ መዝ. 102,24>
❖ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ
ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
❖ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ እና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የበላይ ሓላፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሽዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ሓላፊና
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ጳጳስ
❖ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ ኣብርሀ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ
* ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትልሥራ አስኪያጅ
የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያ ሀላፊዎች እና የድርጅት ሥራ አስኪያጆች
መጋቢ ካህናት ዕንቈ ባሕርይ ተከሥተ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ:
መልአከ ምሕረት አባ ገ/መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ
* የመንበረ ፓትርያርክ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብክት የሥራ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች፣
የ8ቱ ክፍላተ ከተማ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ አበምኔቶች እና ሠራተኞች እንደዚሁ ለዚህ ታላቅ በዓል እንኳን አደረስዎት ለማለት በዚህ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት አንግዶች በሙሉ እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ አሸጋገረን
አሽጋገራችሁ፡፡
በርእሱ እንደተገለጸው “ለትውልደ ትውልድ ዓመቲከ” (ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው) “አቤቱ አንተ አስቀድመህ ምድርን መሠረትክ ሰማያትም የእጅህ ሥራዎች ናቸው እነርሱ ይጠፋሉ
አንተ ግን ትኖራለህ ሁሉ እንደልብስ ያረጃል እንደመጎናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ ይለወጡማል አንተ ግን ያው አንተ ነህ” ዓመታቱ ለልጅ ልጅ እንደሚተላለፍ የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚኣብሔር ዘመናትን እንደልብስ እየቀየረ ዘመናትን እየለዋወጠ እንደሚኖር ልበ አምላክ ዳዊት በመዝ 102 4 24 ነግሮናል፡፡
ልበ አምላክ ዳዊት ዓመቶቹ ለልጅ ልጅ የሆኑትን አምላክ በእየምክንያቱ ያመለጥን እንደነበር ሁሉ እኛም ለዘመኑ ጥንት ለመንግሥቱ ተፍጻሜንት የሌለው የዘመናት ባለቤት ልዑል
እግዚአብሔር ቅዱስነትዎን በሕይወት ጠብቶ በክብር ላይ ክብር በጸጋ ላይ ጸጋ ጨምሮ ክብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከእኛም ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቾዎ ጋር ዛሬ ላይ ስለአደረስን
ከቅዱስነትዎ ፊት ቆመን የዘመናት ባለቤትን እያመሰገን እንኳ ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ አሸጋገረዎ በማለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የምንገኝ የገዳማትና የአድባራት
አስተዳዳሪዎች አበምኔቶች የእንኳን አደረስም የደስታ መግለጫችንን ስናቀርብ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ያለፈውን ዘመን የምንሰናበትበት አዲሱን ዘመን ደግሞ የምንተዋወቅበት ዕለት ነው፡፡
ጳጒሜን ደግሞ አሮጌው ዘመን መንበሩን ለቆ ለመሄድ ሲያኮበኩብ ዐዲሱ ዘመን ደግሞ መንበሩን ለመረከብ ሲስናዳ መሸጋገሪያ ድልድይ በመሆን አገልግሎት ሰጥታ አልፋለች፡መስከረምም
ሓላፊውን ዘመን ለአዲሱ ዘመን ስልጣኑን ከነሙሉ ክብሩ የሚያስረክብበት ወር በመሆኑ ስለመስከረም ወር ጥቂት ማለት እንፈልጋለን ዝ ወርኅ ቀዳማየ አውራኅ ይኩንከሙ ወአቅድምዎ እምአውራኅ ዓመት ::
ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ የዓመቱ መጀመሪያ ይሁናችሁ ዘጸ 12፣2፣ ተብሎ ለእስራኤል ዘሥጋ ቢነገርም ሥነ ፍጥረታዊ ምሥጢሩ ግን በሥነ ፍጥረት ምሕዋር ለምትመራው ቅድስት ኢትዮጵያ ነው በሥነ ፍጥረት ምሕዋር ከዋከብት ዘመናት ማዕዘናት መፈራረቆች ወሮች ሳምንታት ዕለታትና ሰዓታት በየቁጥራቸው ፀንተው ይኖራሉ ዘፍ 114 1:14-20:: በዚህም
መሠረት ግዕዛን ካለው ከሰው ልጅ ይልቅ ልብና ኅሊና የሌላቸው ፍጥረታት በታዘዙት መሠረት ሥራቸውንና ሥራታቸውን ይጠብቃሉ እነሆ ሌሊት ትእዛዟንና ግብሯን ጠብቃ ቀንን ትከተለዋለች ፀሐይም በታዘዘው መሠረት ጨረቃን ይከተለዋል በመጽሐፍ እግዚአብሔር
ትእዛዝ ሰጣቸው ከእርሱም አላለፉም እንደ ተባለው: መዝ 147 16
ወበይእቲ ዕለት አነብሮ ለኅሩየ ዚአየ በማዕከሎሙ ወእዌልጣ ለሰማይ ወእገብራ ለበረከት ወብርሃን ዘለዓለም ወእዊልጣ ለየብስ ወእገብራ ለበረከት፡፡ በዚያችም ቀን እኔ የመረጥሁትን
በመካከላቸው አኖረዋለሁ ሰማይን እለውጣታለሁ ለዘለዓለምም ለበረከትና ለብርሃን አደርጋታለሁ ምድርንም አለውጣታለሁ ለበረከትም አደርጋታለሁ ሄኖ 12 15-17 ነቢየ ልዑል
ሄኖክ በተሰጠው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ከፈጣሬ እስከ ፍጡር : ከሰጭ እስከ ተቀባይ : ሥነ ፍጥረትን ከመነሻው እስከ መድረሻው ሑረቱንና አነዋወሩን ፣ ከጸጋ አስከ ባሕርይ ያለውን ምሥጢርና ግብረ ሥምረት በዚህ ጥቅስ ጠቅልሎ እንዲህ ገልጾታል።
ይህ ቃል
1ኛ የፍጥረታት ባለቤት የልዑል እግዚአብሔርን ሥልጣንና መግቦት፡፡
2ኛ. በፍጥረታት ላይ አለቃ ሁኖ የተሽመ አበፍጥረት አዳምንና ጸጋውን፡፡
3 ርእሰ ዓውደ ዓመትን
4ኛ ከርስቶስ በተዋሕዶ የሠራውንና ለሰው የሰጠውን ማዳንና ክብር
5ኛ በእግር የተከተሉት በግብር የመሰሉት ዛሬም ይሆን መንፈሳዊ መዓርግ በቅብብሎሽና በአደራ ተረክበው ውሉደ ቤተክርስቲያንን በመንፈላዊ መግቦት የሚመሩ የሚያስተምሩ አበው
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን የሚገልጽ ቃል ነው ::
ወፈጠረ ኩሎ ግብረ በከሂሎቱ : ᎓᎓ በልዩ ከሂሎቱ በሰማይ በምድር ያሉ የሚታዩ የማይታዩ ፍጥረታትን አስገኘ ᎓᎓ዮሴፍ ወልደ ኮር 12:22
መስከረም ወር ከአፍ እስከገደብ ሞልቶ የነበረው ጅረት ሁሉ ከሙላቱ የሚጐድልበት ጎርፍም ሆነ ዶፍ ፀጥ ረጭ የሚልበት ደፍርሶ የከረመው ውሃም ነጭ ባዘቶመስሎ ጠርቶ የሚታይበት
በደመና ተሸፍኖ ለወራት የቆየው ሰማይም የተወለወለ መስተዋት የሚመስልበት ጋራ ሽንተረሩም በተለያዩ የአበባ አይነቶች ተውቦና አጊጦ ደምቆና አሸብርቆ የሚታይበት ፀሐይም ብርሃኗን የምትፈነጥቅበት እና ዐዳዲስ ነገሮች የሚታዩበት ወር በመሆኑ የዘመናት መሸጋገሪያ እና የዐዲስ ዓመት መጀመሪያ ለመሆን በቅቷል።
ብፁዕ ወቅዱስ ባታችን
ምእመናን በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር እንዲጸኑ የምእመናን አንድነት እንዲጠነክር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት የተሟላ እንዲሆን የአገልጋዮች ካህናት ኑሮም የዘለቄታ
ዋስትና እንደኖረው እና ከሁሉ በፊት የትምህርተ ወንጌልን መጠናከር እና መስፋፋት አማራጭ የሌለው መሆኑን አስቀድመው በመገንዘብዎ በቅዱስነትዎ አርቆ አሳቢነት የምሁራን ምንጮች የሆኑት ከፍተኛ የመንፈሳዊ እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲጎለብቱ በመደረጉ በአገራችን ቀደም ብሎ የተከሠተው የሃይማኖት ወረርሽኝ በአሁኑ ስዓት እየተገታ ይገኛል: ምን ጊዜም ቢሆን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዓለም የምታበሥረው እና የምታውጀው በትምህርተ ወንጌል ነው፡፡ ስለሆነም ዓለም እርስ በርስ ሲተራመስ በዕሳትና በስለት ሲተላለቅ የሚኖረው ለሰላም በተፈጠረው ለሁሉም ሊበቃ በሚችለው ስፊ ዓለም በጋራ ለመኖር የሚያስችለው የፍቅር ጥበብ በማጣቱ እንደሆነ ቅዱስነትዎ በየጊዜው የሚያስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱን ያኮራ የመንፈስ ልጅዎችዎን እጅግ ያስደሰተ ነበር አምላክ ዛሬም በቅዱስነትዎ ላይ አድሮ እጅግ አስደናቂና አስገራሚ የሆኑ ሥራዎችን ሠርቶ አሠርቷል።
በመሠረቱ የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስነትዎን በዚህ ቅዱስ መንበር ላይ ካስቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስነትዎ በሳል አመራር ሰጭነት ያልተሠራ መልካም ሥራ ባይኖርም በዘመነ ክህነትም የተሠሩ ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራት እጅግ በርካታ ከመሆናቸው የተነሣ ዘርዝሮ ለማቅረብ ከመሞከር ይልቅ ብዛታቸውን ለቤተ መዛግብት ትቶ ማለፍ እንደሚቀል ተገንዝበናል።
በዚህም ዘሩያ ያለፈውን በመዘርዘር የወደፈቱን በመጠቆም ሰፋ ያለ መግለጫ ማቅረብ ይቻል ነበር ነገር ግን ባለፈው ዓመት የሠሩትን አኩሪ ታሪክ የፈጸሙትን ተግባር ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ እና የዓመቱን አጠቃይ የሥራ ክንውን በዚህ አጭርና ጠባብ ጊዜ መግለጽ ስለማይቻል ለዓመታዊ ሪፖርት አቀራቢዎች ትተን ለማለፍ ተገደናል።
ቅዱስነትዎ፡- ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምንና ዕርቅን ፍቅርናና እንድነትን ከማስተማር ውጭ የተለየ ዓለማና ጥሪ እንደሌላት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ያልገለጹበት ጊዜ የለም በአሁን ጊዜም ከእኛ አልፎ ተርፎ የቅዱስነትዎን ቡራኬ ዓለም በሙሉ እየተቋደሰ ይገኛል ስለዚህ የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ለቅዱስነትዎ
ረጅም ዕድሜና ጠንነትን እንዲሰጥልን የዘወትር ምኞታችን ነው እኛም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቾዎ ከቅዱስነትዎ ጎን በመቆም በየጊዜው በቅዱስነትዎ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ
ሓላፊዎች የሚሰጠንን መመሪያና ትእዛዝ ሁሉ ተቀብለን ተግባራዊ በማድረግ ከምን ጊዜውም በበለጠ ተግተን እና ነቅተን ለመሥራት ቁርጠኝነታችን በመግለጽ ለቅዱስነትዎ አዲሱ ዘመን
የሰላም፣ የፍቅር፣ የልማት, የአንድነት የጤንነት ዘመን እንዲሆንልዎ እንመኛለን።
የብፁዕ ወቅዱስነትዎ ቡራኬ ይደረሰን!!!
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና አበምኔቶች!
መስከረም 3 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ