የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለፉት 100 ቀናትና ሥራዎቹ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚገኙ ጥንታውያት አህጉረ ስብከት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ነው።
ሀገረ ስብከቱ በሥሩ 8 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት፣ ከ260 በላይ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከ30,000 በላይ አገልጋዮችና ሠራተኞች፣ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰንበት ተማሪዎች፣ እጅግ ብዙ ደጋግ ኦርቶዶክሳውያን የሚገኙበት ታላቅ ሀገረ ስብከት ነው።
ሀገረ ስብከቱን በርካታ ብፁዓን አባቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በተለያዩ ጊዜያት በአባትነት አገልግለዋል መርተውታል።
ከነዚህ መካከል ባሳለፍነው ዓመት 2017 ዓ/ም በግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የተመደቡትና ሀገረ ስብከቱን እየመሩ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ አንዱ ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከተመደበቡት ጊዜ ጀምሮ ሥራዎችን በሦስት ወራት ዕቅድ በመከፋፈል እየሠሩ ይገኛሉ።
ከነዚህ በመጀመሪያ ሦስት ወራት ወስጥ እንዲሠሩ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ያደሩና የሰነበቱ ሥራዎች መካከል በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተወሰነላቸው የ150 ተፈናቃይ አገልጋዮችን ሥራ መመደብ፣ የሀገረ ስብከቱን ዋና መሥሪያ ቤት ከሊቀ ጳጳስ ቢሮ ጀምሮ ያሉ ቢሮዎች ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ ማደስና የአስተዳደር ችግር የተፈጠረባቸውን አብያተ ክርስቲያናት መፍትሔ ሰጥቶ ማቃናትና የሀገረ ስብከቱ የአሠራር መንገድ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ማዘመን የሚሉ ጉዳዮችን ዋነኛ ዓላማዎች በማድረግ ሥራዎች ላለፉት 100 ቀናት ሲሠሩ ቆይተዋል።
ይሄንን አስመልክቶም በብፁዕነታቸው መሪነት በተከናወነው በበትናትናው ዕለት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አደራሽ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ መጋቤ ትፍስሕት ሙሉጌታ ቸርነት የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎች ፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት በተገኙበት የሚመለከታቸው የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሐላፊዎች በተገኙበት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል።
የ100 ቀናት ሪፖርቱ ዋና ጸሐፊው በመጋቤ አእላፍ ማሙየ ሸዋፈራው በአጠቃላይ በአሠራርና አሁናዊ እንቅስቃሴዎች ፣ ሊቀ ኅሩያን ባዩ ተዘራ የሰው ኃይል አስተዳዳር ዋና ክፍል ሐላፊ ከሥራ ሰዓት አከባበርና አገልጋዮች ለተሰጣቸው ሥራ ያላቸውን ቅርበት እንዲሁም ከቅጥርና ከዝውውር ከእድገት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲሁም ሊቀ ኅሩያን አስናቀ ሽዋዬ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሐላፊ የሒሳብ ጉዳዮችን በተመለከተ ሪፖርት አድርገዋል።
የተሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች
የቢሮ አካባቢን ምቹ ከማድረግ ጋር ተያይዞ በብፁዕነታቸው አማካኝነት የመጡ ስማቸው ሊጠቀስ ያልፈለጉ በጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳዊ የብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን ቢሮ ሙሉ ዕድሳት በማድረግ የሀገረ ስብከቱን ጥንታዊነትና ግዙፍነት እንዲሁም ለአገልጋይና ተገልጋይ ምቹ ሁኔታን በሚፈጥር መልኩ ለማደስ ተችሏል። ከዚህ ጋር ሙሉ የውስጡ ቢሮዎች የቀለምና የመውረጃና መውጫ ድጋፍ ብረቶች በጠንካራ ብረት እንዲቀየሩ ተደርገዋል።
በሀገረ ስብከቱ ቢሮዎችና በግቢው ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች ከሕሊናና ከሕጋዊ አሠራር ያለፈውን ለመከታተልና የግቢውን ደኅንነትና ሥርዓት ለመጠበቅ እንዲሁም የግልጸኝነትን አሠራር ለማጠናከር በማሰብ የደኅንንነት ካሜራዎች በሁሉም አቅጣጫ እንዲገጠሙ ተደርጓል። በዚህም ግብረ መልሱ እጅግ የሚበረታታ ሆኖ ተገኝቷል።
ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ውጭ የሚደረጉ ድርጊቶችን በቀኖናና አስተዳደራዊ ርምጃ ተግባራዊ በማድረግ ሥርዓትን ለማስጠበቅና ተግባራዊ ትምህርት ለመስጠት ተሠርቷል።
ሀገረ ስብከቱ ምንም እንኳ ዝውውር ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል ብሎ ባያምንም ችግሩ በዘላቂንት ለማስተካከል መደላድል እና ጊዜያዊ መፍትሔ ይሆናል በሚል በተለያዩ ምክንቶች የአስተዳደር ችግር የተስተዋለባቸውን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ዝውውር ተደርጓል።
በዚህም የከረሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እፎይታ ከመስጠት ጎን ለጎን የተመደቡት አካላት በተመደቡባቸው አብያተ ክርስቲያናት በአዲስ ኃይልና መንፈስ እንዲሠሩ መደላድል ለመፍጠር ተችሏል።
በዚህም
-34 አስተዳዳሪዎች
-20 ዋና ጸሐፊዎች
-8 ዋና ቁጥጥሮች ዝውውር ተደረጎላቸዋል።
በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የኮንትራት ጊዜው ያለፈውን የጥበቃ አቅራቢ ድርጅት በሕጋዊ መልኩ በመቀየር በሌላ የጥበቃ የሰው ኃይል አቅራቢ ድርጅት እንዲተካ ለማድረግ ተችሏል። ከዚሁ ጋር ተገልጋይ ማመልከቻውን የሚያስገባበት ቢሮና አሠራር ለመተግበር ዝግጅቱ ተጠናቆ በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል።
በ100 ቀናት ውስጥ የተፈናቀሉ አገልጋዮችን ወደ ቦታ የመመስና ሥራና ደሞዝ እንዲኖራቸው ከማድረግ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በእጅጉ የሚበረታቱ ሲሆኑ መቶ ሃምሳ ተብለው ከሚጠቀሱት ተፈናቃዮች ያልተመደቡ 57፣ ተመድበው የአብያተ ክርስቲያናቱ ሰበካ ጉባኤ ያልተቀበሏቸው 45 እንዲሁም በሁለተኛ ዙር ከተላከው በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ አገልጋዮች ዝርዝር 98 በአጠቃላይ 200 አገልጋዮች ሲሆኑ ከነዚህና የገዳማትና አድባራት ሰበካ ጉባኤ በቀረበ የይጽደቅልን ጥያቄ በማካተት በ100 ቀናት ውስጥ #159 አገልጋዮች ተመድበዋል የአገልግሎት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተካሔደው የሰነድ ማጣራት ትክክለኛ ሰነድ አሟልተው ያቀረቡና የሥራ መደብ የሚፈልጉ 104 ብቻ አገልጋዮች ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተመረጡ አብያተ ክርስቲያናት በክፍት በጀት ወይም አዲስ በጀት እየተከፈተ የሚመደቡ ይሆናሉ።
በዚህ አሠራር ከፍተኛ ተግዳሮት የተስተዋለበትን የውስጥ መንፈሳዊ አገልጋዮች (ስብከተ ወንጌል፣ ማኅሌትና ቅዳሴ) ወደ ቢሮ የሚያደርጉትን ፍልሰት በተቻለ አቅም ለመቀነስ ተሞክሯል።
በአጠቃላይ ባለፉት 100 ቀናት ለተሻለ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ከማደላደል አንጻር በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ተሞክሯል።
ይሁን እንጂ ባለፉት 100 ቀናት ምክንያታቸው የዋለ ያደረ ቢሆንም ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸው አልቀረም።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሪነት ተከታታይነትና የዓላማ አስቀጣይነት ጉዳይ ላይ በብዙ የሚፈተን ሀገረ ስብከት በመሆኑ የነበረውን መልካም ተሞክሮ ከማስቀጠል ይልቅ ነቅሎ መተካት የሚመሥሉ መንገዶችን ሲከተል ይስተዋላል።
በመሆኑም ይህንን ችግር እያረሙና በመጠኑም እያስተካከሉ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ከትናንት የተላለፉትን መልካም ሥራዎችና ዓላማዎችን በማስቀጠል የሚስተካከሉትን ደግሞ በማረም የማይቋረጠውን የቤተ አገልግሎት ማስቀጠል የአደራ ግዴታ ነው።
ስለሆነም በሀገረ ስብከት ጀምሮ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት በይበልጥ ደግሞ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መዋቅራዊ መናበብን የሚፈታተኑና ተጠያቂነትን የሚያመጡ ሕገ ወጥ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ባለፈው 100 ቀናት የታዩ ችግሮች ናቸው።
ከነዚህም
➡️ የራስ አገዝ ልማቶችንና ለሕያው አገልግሎት ድጋፍ ይሆን ዘንድ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚሠሩ ልማቶች የሚከራዩ ቦታዎችና ሡቆች ዘለቄታዊነት ባለው መልኩ ካለመሠራቱ ባለፈ ወጥነት በሌለው የውል ኪራይ ከሕግ ውጭ ለበርካታ ዓመታት ማከራየት፤
­➡️ የቤተ መቅደሱና የዐውደ ምሕረቱ አገልጋዮች ከዋናው መንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ቢሮ ለመግባት የሚደረገው ፍልሰት መኖሩ፤
➡️ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች ላይ የሚፈጸም ሕገወጥና መስመሩን ያተለከተለ ርምጃ መኖሩ ለብዙ ተፈናቃዮች ምክንያት ሆኗል።
➡️በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መደበኛ የሥራ ጊዜን በአገባቡና ለተሾሙበት የቤተ ክርስቲያን ሐላፊነት አለመጠቀም በሳምንት ሁለት ቀናትና ብቻ ወደ ቢሮ የሚገቡ የአስተዳዳር ሠራተኞች መበራከት ፣
➡️በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መተዳዳሪያ ደንብ አንቀጽ 13 ቁጥር 7 ላይ እንደተቀመጠው “የመቅጠር የማዘዋወርና ዕድገት የመስጠት ሥልጣኑ” የሀገረ ስብከት ሆኖ እያለ ለብዙዎች መፈናቀል፣ መንገላታትና ችግር ላይ መውደቅ ምክንያቱ የሆነው በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚፈጸም ሕገወጥ ቅጥርና ዕድገት መኖሩ ፣
➡️ሀገረ ስብከቱ ክፍት በጀት ባለቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሠራተኞችን ሲመድብ አልቀበልም የሚሉ ገዳማትና አድባራት አስዳዳር ጽ/ቤቶች መኖራቸው፤
➡️በቃለ ዓዋዲው የተገለጸውን የሀገረ ስብከት ድርሻ 20 ፐርሰንት ላለመክፈል ገቢን መሰወር በተቃራኒው ከሕግ ወጭ የሆነ ገንዘብ ሲጠየቅ እንዲወጣ መፍቀድ፤
➡️በሕጋዊ ደረሰኝ አጠቃቀም ዙሪያ በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት የሚታየው ብልሹና ሕገወጥ አሠራር በዋናው ወይም በበራሪው ላይ ካርቦን ባለመጠቀም የተለያዩ የገንዘብ መጠኖች በመጻፍ ለግል ጥቅምና ማዋል ይህም ብልሹ አሠራር በአሁኑ ሰዓት መልኩን ቀይሮ የባንክ ስቴትመንት ጭምር ፎርጅድ በማሠራት ያልተከፈለ ፐርሰንትን እንደተከፈለ አድርጎ ማሳየትና ከፍ ብሎ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱን ጭምር በማሳሳት ደረሰኝ ማስቆረጥ፤
➡️ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የልማት ሥራዎች ያለ ሕጋዊ ጨረታ የፋይናንስ ሕጉን ሳይጠብቅ ያለ ውድድር በአንድ ግለሰብ ብቻ በሚቀርብ የሥራ ዋጋ ማሠራት ፤
➡️የቤተ ክርስቲያኑን አቅም ያላገናዘበ የደሞዝ ጭማሪ ማድረግና ተገቢነት የጎደለው ከደመወዝ በላይ የሆነ ከፍተኛ አበል እንዲከፍል ማድረግ የሚሉ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶችና ችግሮች ናቸው።
በመሆኑም ሀገረ ስብከቱ ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮችን ለመፍታት ይችል ዘንድ ዘመኑን የዋጁ አሠራሮችን በጥናትና በምክክር በማዳበር በአጭር ጊዜ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል። ከዚህ ሲያልፍ ቀጥተኛና የማደግም ሕጋዊ ርምጃ በሐላፊነት በተሰጣቸው አካላት ላይ የሚወሰድ ይሆናል።
በተለይም የሀገረ ስብከቱን መዋቅራዊ የበላይነት የሚገዳደሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ገቢ በሕግዊ መንገድ የማይሰበስቡና ውጪውንም በማይቆጣጠሩ እንዲሁም ከሕግ ውጭ ባልተሰጣቸው ሥልጣን አገልጋዮችን በእፎይታ ውስጥ ሆነው እንዳያገለግሉ በሚያደርጉ አስተዳዳሪዎችና የሥራ ሐላፊዎች ሀገረ ስብከቱ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወስድ ሁሉም አካል ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ በቀጣይ የ100 ቀናት ዕቅዶች የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማስቀደም የተሻሉ ሥራዎችን በመሥራት ችግሮችን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን ችግሮች እንዳይከሰቱ የሚያስችል ተጠያቂነት መሠረት ያደረገ አሠራርን ለመዘርጋት በዕቅድ ተይዟል።
ከነዚህም
ለአስተዳዳሪዎችና ለጸሐፊዎች ፣ ለቁጥጥሮችና ለሒሳብ ሹሞች እንዲሁም ለምክትል ሊቃነ መናብርትና ለሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮች ተከታታይነት ያለው ሥልጠና ይሰጣል፤
ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች በአበል ምክንያት የሚስተዋለውን ከፍተኛ ችገር ለመቅርፍ ይቻል ዘንደ ወጥነት ያለው ሕጋዊ የሆነ ወቅቱንና ዘመኑን የዋጀ የደመወዝ ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል ።
የመንፈሳዊ አገልጋዮች ወደ ቢሮ የመፍለስ ሁኔታን ለመቀነስና ለማስቆም ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ካህናትና ዲያቆናት በአጠቃላይ በስብከተ ወንጌል በማኅሌት በቅዳሴ ለሚያገለግሉ አገልጋዮች ብቻ መሠረት ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ በጋራ ጥናት ተግባራዊ ይደረጋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረውና ብዙ መጉላላትን ያስከተለው በተለምዶ አሮጌው ቄራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የሚገኘው የሀገረ ስብከቱ ሁለገብ ሕንጻ በተፈጠረው የግንባታ ችግር ምክንያት በርካታ ውይይቶች የተደረገበት ሲሆን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን ሁለም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ትብብርና ድጋፍ ማድረግ የሚገባቸው ትልቅ ጉዳይ ነው ተብሎ በእጅጉ ይታመናል።
በመሆኑም ከአሮጌው ቄራ ሁለገብ ሕንጻ በተጨማሪም በኪራይ የሚገኙትን የየክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችን ከኪራይ አላቆ የራሳቸው የሆነ ቢሮና ሕንጻ እንዲኖራቸው የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ለሁነኛ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ በመፋጠን የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀምና አደራን በመወጣት ብርሃን ሳለ በብርሃን በመመላለስ እውነተኛ ሥራ የመሥራት የሁሉም አገልጋይና ተገልጋይ ድርሻና መንፈሳዊ ግዴታ በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማል በሚል መንፈስ ሁሉም ተልእኮውን እንዲወጣ ሀገረ ስብከቱ በጽኑዕ ያሳስባል።