ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የቦሌ ቡልቡላ ፍኖተ ሕይወት ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና ሐዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የቦርድ ሰብሳቢ ዛሬ መስከረም 22/2018 ዓ.ም የቦሌ ቡልቡላ ፍኖተ ሕይወት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት እየገነባ የሚገኘውን አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ ።
የደብሩ የአገልግሎት መሪዎች እየተገነባ በሚገኘው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው በሰሙትና ባዩት የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ የእጅግ የሚበረታ መሆኑ ገልጸው በተጠናከረና በተናበበ መልኩ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
አክለውም በዋናው የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለማስፈጸምና ለአገልግሎቱም መደላድል ለመፈጠር የሚሠሩ የራስ አገዝ ልማቶች ጊዜውን፣ የቦታውን ሁኔታና ዘለቄታዊነትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ጠንከሮ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና ብፁዕነታቸው በዛሬው ዕለት የቡልቡላ ምስካበ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የማጠናቀቂያ ሥራዎችን ግብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ከብፁዕነታቸው ጋር መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ኅሩያን ይልማ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ፣ የደብሩ አስተዳዳሪና ዋና ጸሐፊ እንዲሁም ማኅበረ ካህናት ተገኝተዋል።