“በጋራ በመወያየት ችግሮችን መፍታትና የተሰጠንን ሐላፊነት ለቤተ ክርስቲያን ለጥቅም ማዋል እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ አሳሰቡ
በጋራ በመወያየት ችግሮችን መፍታትና የተሰጠንን ሐላፊነት ለቤተ ክርስቲያን ለጥቅም ማዋል እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ አሳሰቡ።
ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባዘጋጀው የሥልጠናና የምክክር መርሐ ግብር ላይ ነው።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከመስከረም 26_30/2018 ዓ/ም ለተከታታይ 5 ቀናት ለሀገረ ስብከቱ፣ ለክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እንዲሁም ለገዳማትና አድባራት የሥራ ሐላፊዎችና ሠራተኞች ያዘጋጀው የሥልጠናና የምክክር ጉባኤ በዛሬው ዕለት በብፁዕ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና የሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና መጋቤ ትፍስሕት ሙሉጌታ ቸርነት የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተገኝተዋል፡፡
በዛሬ የሥልጠናና የምክክር መርሐ ግብር የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ሐላፊዎችና ምክትሎች፣ የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆችና የሰው ኃይል ክፍል ሐላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ የሀድያ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሥልጠናው አሠራሮችን ለማሻሽል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው “ ትንንሽ ሥልጣኖች አሉን ብዙ ሰዎች የምንረዳበት ፤ ብዙ የተራቡ አንጀቶች ፤ በኛ ምክንያት እንዲጠግቡ ምክንያት መሆን እንችላለን ፤ ርህራሄው በጎነቱ ሲኖር ህሊናችን ሰላም እና ዕረፍት ያገኛል” ብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አክለውም እንኳን ለአስተዳዳር ሥራ ለመጽደቀም መመካከር ይጠቅማል ያሉ ሲሆን እየተወያየን እየተነጋገርን እየተግባባን ፤ በሄድን ቁጥር ብዙ ችግረኞችን ፤ ብዙ ካህናትን ብዙ ሊቃውንትን ፤ በየደጀ ሰላሙ የወደቁ የቤተክርስቲያኒቱን ምሁራንን ቀና ማድረግ ማንሳት እንችላለን ፤በተቻለ መጠን ውይይታችን መቀራረባችን ይህ ሥልጠና ዘመናዊ አሠራርን ማስፈን የበለጠ እየጠነከረ ቢሄድ ይጠቅማል” በማለት ገልጸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ትምህርትና ማስልጠኛ ዋና ክፍል ሐላፊ መልአከ ገነት አባ ተክለ ማርያም አምኜ የሥልጠና ምንነትን ያብራሩ ሲሆን ሥልጠና የለውጥ መጀመሪያ፤ የሥራ ማነቃቂያ የውጤት መጓዣ ሐዲድ ነው። ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ተቋም ዘወትር ይማራል፣ ፣ይወያያል፣ ይገመግማል፣ ምርቱን ከገለባው ይለያል፣ በድክመቱ ማስተካከያ በጥንካሬው በርታ የሚያስብለውን አሠራርን ይዘረጋል ብለዋል።
ቀጥለውም ዛሬ የተጀመረው ሥልጠናና የምክክር ጉባኤው በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ሐሳብ አመንጭነትና መሪነት የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም በዋነኛነት ለተቋማችን የጋራ ተቀርቋሪነትና የኔባይነት ኑሮን በእምነትና በእውቀት እንድንሠራ በር መክፈት፤ የጋራ የውጤት ምእራፍ እንዲኖር መግባባትን መሠረት በማድረግ ለለውጥ መነሣት የሚል መሆኑን አብራርተዋል።
በሥልጠና መርሐ ግብሩ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተለያዩ ምሁራን የመነሻ ጥናት አቅርበዋል።
“መልካም አስተዳደር” በዶ/ር ግርማ መኮንን ፣ “ቅጥር ዕደገትና ዝውውር ከሕግ አንጻር” በመልአከ ሰላም በዶ/ር አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ እንዲሁም “በመሬት አጠቃቀምና የውል አሰጣጥ” በአቶ አያሌው ቢታኒ የመነሻ ቀርበዋል።
በቀረበው መነሻ ጽሑፍ ላይ ከተሳታፊዎች ጥናቄዎችና አስተያየቶች የቀረበው ሲሆን ለጥያቄዎቹም ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል።
የሥልጠናውና የምክክር ጉባኤው እስከ መስከረም 30/2018 ዓ/ም የሚቀጥል ሲሆን ከነገ ጀምሮ እስከ ሐሙስ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ የገዳማትና አድባራት የሥራ ሐላፊዎችና የአገልግሎት መሪዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
