“ሃይማኖት በአፍ የሚነገር ብቻ ሳይሆን በልብ የሚታሰብ የምንቀበለው እውነታ ነው።” ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ዓድዋ ሙዚየም ሕንጻ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ፣ ሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ “ሃይማኖት በአፍ የሚነገር ብቻ ሳይሆን በልብ የሚታሰብ የምንቀበለው እውነታ ነው።” በማለት የሃይማኖትን ከፍታ አንስተዋል።
ብፁዕነታቸው የሃይማኖትን ምንነት ከቃሉ የት መጣነት ጠቅሰው አብራርተዋል። አክለውም “ሃይማኖትን ከምግባር ጋራ አስተሳስረን ልንይዝ ያስፈልጋል።” ሲሉ ተግባራዊ ጉዳዮች ላይ ልንይዘው ያስፈልጋል ብለዋል።
ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ሓላፊ “ስለሰላም ለመስበክና ለማስተማር የሃይማኖት ተቋማትን የሚቀድመው የለም።” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ “አሁን ያለንበት ወቅት ከበፊቱ የበለጠ ርብርብ፣ ትብብር ማድረግ አለብን።” ሲሉ ዋና ፀሐፊው አክለው ተናግረዋል።
በዕለቱ ለተለያዩ ተቋማት፣ የቀድሞ የጉባኤው አመራር አካላት፣ ለተባባሪ አካላት የዕውቅናና የምስጋና መርሐግብር የተደረገ ሲሆን፤ በ2017 የበጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ቀርቦ ውይይት እና ምክክር ተደርጓል።
በውይይቱ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ፣ ሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ፣ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቤ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ፀሐፊ፣ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ፣ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የጉባኤው አባላት አመራሮችን ጨምሮ ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት አመራር አካላት ተገኝተዋል ሲል ተሚማ ዘግቧል።
