ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሲገለገሉባቸው የነበሩ ንዋያተ ቅድሳትን በስጦታ መልክ ማበርከታቸው ተገለጸ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚፈጽሙባቸው ንዋያተ ቅድሳትን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፣ለርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፣ ለጭኽ መካነ ሕይወት አጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ እና ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ማበርከታቸው ተገልጿል።
ቅዱስነታቸው በፓትርያርክነት ዘመናቸው ሐዋርያዊ ተግባራትን ከሚያከናውኑባቸው መካከል ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ መስቀሎች፣ አርዌ ብርት፣ በትረ ሙሴ እና የመሳሰሉት ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ምእመናንና ምእመናት እንዲማሩባቸው፤ ትውልድም ታሪኩን ለማወቅ እንዲጠቀምባቸው በማሰብ፡-
1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፤
2. የቤተ ክርስቲያናችን እና የሀገራችን ታሪክ መነሻ በሆነችው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፤
3. በመነኰሱበትና በተማሩበት ጭኽ መካነ ሕይወት አጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ እና ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም
በተዘጋጀላቸው ሥፍራ በክብር ተቀምጠው ጎብኚዎች ይመለከቷቸውና ይማሩባቸው ዘንድ አበርከትዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የበላይ ሓላፊ፤ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ፤ እንዲሁም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ያስረከቡ ሲሆን፤ የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየም መምሪያ ሓላፊና ሠራተኞችም ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እጅ ተረክበዋል፡፡
© የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
