“ቤተ_ክርስቲያን_በዚህ_መልክ አስተምራ ያስመረቀቻችሁ በሌላኛው የሕይወት ገጽ የተማራችሁትን የዓለማዊ ትምህርትና እውቀት እንድትተው ሳይሆን ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጋር አጣጥማችሁና አቀናጅታትሁ ቤተ ክርስቲያን እንድታተርፍባችሁ ነው። ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በሥርዓተ ትምህርት መሠረት ያስተማራቸው 11,885 ተማሪዎች ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ለ5ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
መርሐ ግብሩ ሕያውን የእግዚአብሔር ቃልና ግሩም ግብሩን እንዲሁም ወርኃ ጽጌን የሚገልጹ ዝማሬዎች ፣ ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ እና ስብከት እንዲሁም በብፁዓን አባቶች ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶበታል።
በዛሬው ዕለት የተመረቁ ተማሪዎች ከ164 ገዳማት እና አድባራት የተውጣጡ የሀገረ ስብከቱን ምዘና ወስደው ወደ ቀጣይ ክፍል የተዘዋወሩ 11,885 የሰንበት ት/ቤት የ4ኛ፣ የ8ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ላእከ ኄራን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አድነት ተቀዳሚ ምክትል ሰብሰቢ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በ8 የትምህርት ዘርፎች የተከፋፈለውን ሥርዐተ ትምህርት መሠረት በማድረግ በየገዳማቱና አድባራቱ ባሉ ሰንበት ት/ቤቶች ቅዳሜና እሑድ ትምርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አስተውሰዋል።
አክውለም በዚሁ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከቱ ድጋፉና የኔባይነቱ በእጅጉ የሚያስመሰግን ሲሆን የዛሬውን የምርቃት መርሐ ግብር አስፈላጊ በሆነው በጀት በማገዝና የሥርዐተ ትምህርቱ መጻሕፍትን አጥቢያዎች ለየሰንበት ትምህርት ቤቱ እንዲገዙና ከማድረግና የምዝና ፈተና በሚሰጥበትም ወቅት ከብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ በየቦታው በመዘዋወር ምልክታና ክትትል በማድረገቸው በእጅጉ ኮርተናል በልጅነት ልብም እናመሰግናለን ብለዋል ላእከ ኄራን መንክር ግርማ።
በመርሐ ግብሩ ለ160 ሰንበትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተመራቂ ተመራቂዎች፣ ሰንበት ት/ቤቶች እና ክፍለ ከተሞች ከአባቶች እጅ ቡራኬና
ሽልማት ሲቀበሉ የጀሞ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ዋንጫውን ወስደዋል።
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ ተመራቂ ተማሪዎቹ ትምህርቱን በአግባቡ እንዲከታተሉ ዘወትር በመማርና በማንበብ እንዲተጉና ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሆነው እንዲቆሙ አሳስበዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቁነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባዩት መልካም ቤተ ክርስቲያናዊ ትልቅ ተግባር ተደንቀው የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በትውልድ እንዲጸና የተቀበሉትንም የእምነትና የእውቀት ቤተ ክርስቲያናዊ አደራቸውን እንዲጠብቁ ተመራቂዎችን አሳስበዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን በዚህ መልክ አስተምራ ያስመረቀቻችሁ በሌላኛው የሕይወት ገጽ የተማራችሁትን የዓለማዊ ትምህርትና እውቀት እንድትተው ሳይሆን ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጋር አጣጥማችሁና አቀናጅታትሁ ለቤተ ክርስቲያን እንድታተርፍባቸው መሥራት ይኖርባችኋል በማለት በአጽንኦት አሳስበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በዚህ ሁሉ አገልግሎት ለሚታይ ቤተ ክርስቲያናዊ ስኬት በማድረስ ረገድ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ ሊመሰግኑ ይገባል የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍልና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መሪዎችና አስተባባሪዎችንም በእጅጉ እናመስግናልን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ አባቶቻችን የተረፋቸውን ሳይሆን ያላቸውን ሳይቀር ሳይሰስቱ ሰጥተው ያስረከቡንን ቤተ ክርስቲያን በእምነትና በእውቀት በመታዘዝ የተማርነውን ለሕይወት ዋጋ ማድረግ ይገባለናል በማለት ለተመራቂዎች መልእክት አስተላላፈዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምጦስ የመንበረ ፓትርያርክ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሊቃነ መናብርት፣ የሰንበት ት/ቤት አመራሮች፣ መዘምራንና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝቷል።