ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ጥር ፲፯/፳፻፲፯ ዓ/ም ሐዋርያዊ ጉብኝት አደረጉ።
በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ደብሩ ለሰንበት ትምህርት ቤት መገልገያ እንዲሆን የሚገነባው ባለሁለት ወለል (G+2) ሕንጻ መሠረት ድንጋይ ባርከው አስቀምጠዋል።
ከዚሁ ጋር ደብሩ ለጸበል አገልግሎት እንዲሰጡ ገንብቶ ያጠናቀቃቸውን 12 ክፍሎች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ብፁዕነታቸው በደብሩ የተሠሩ የቅድስናውን አገልግሎት የሚደግፉ የራስ አገዝ ልማቶችን አድንቀው በቀጣይ የደብሩ ማስተር ፕላንን አሠርተው በሀገረ ስብከቱ በማጸደቅ ትውልዳዊ ድርሻ ያላቸውን ሥራዎች እንዲሠሩበትና ቦታውንም በሚጸድቀው ፕላን መሠረት እንዲጠቀሙ መመሪያ አስተላልፈዋል።
አክለውም በደብሩ የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተሠርተው እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የኮልፌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን ገቦረ ሥላሴ በበኩላቸው ስለደብሩ በብዙ መልኩ አርአያነቱ የጎላ መሆኑን አስታውሰው በራስ አገዝ ልማት እንቅስቃሴም የደብሩ አስተዳዳርናና ሰበካ ጉባኤን አመስግነዋል።
በተያያዘም የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሃይማኖት ኢሳይያስ ቸርነት ደብሩ ከተመሠረተ ከ35 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰው የካህናቱን የአገልግሎት ትጋት፣ የራስ አገዝ ልማት እንቅስቃሴውንና የሕዝቡን ታዛዥነትና መልካም ናፍቆት መሠረት በማድረግ ደብሩ የካቴድራልን ስያሜ እንዲሰጠው ባቀረቡ ጥያቄ መሠረት ብፁዕነታቸው “የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል”ተብሎ እንዲጠራ ፈቃድ ሰጥተዋል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ