ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በመንፈሳዊ ሥርዓትና በሰላም መከበራቸውን አስመልክተው የምስጋና መልእክት አስተላለፉ
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በመንፈሳዊ ሥርዓትና በሰላም መከበራቸውን አስመልክተው የምስጋና መልእክት አስተላለፉ።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በልዩ ሥርዓትና በዐደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በእጅጉ ተጠቃሾች ናቸው።
በዓሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነትና የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱንና መጠመቁን እንዲሁም ጌታ ከገዳመ ቆሮንቶሰሰ የ40 ቀናት ቆይታ በኋላ በሦስተኛው ቀን በገሊላው ቃና መንደር በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠበትና የመጀመሪያውን ታላቅ ተአምር ያሳየበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በዓላት ናቸው።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕያው የመዳን ታሪክን መነሻ በመድረግ ለእውነተኛ በረከት ለመንፈሳዊ ጽንዐት ለይቅርታ እንዲሁም የክርስቶስን የማዳን ሥራ ለመመስከር በልዩ ሥርዓትና ድምቀት ከጥምቀት ዋዜማ ከተራ ጀምሮ ታከብረዋለች።
ቅዱስ ቄርሎስ በቅዳሴው እንዳመሰገነው “ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቤተ ክርስቲያንህ ትሰግድልሃለች፣ ሙሽራህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች”(ቅዳሴ ዘቄርሎስ ቀ.፵፱)ኀ እንዳለው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በዓደባባይ ወጥታ መገለጡ ለመስበክ ታቦታቱን ባከበሩ ካህናት፣ በአባቶች ቡራኬ፣ በካህናቱ ማእጠንት፣ በሊቃወንቱ ምስጋና በወጣቶች ዝማሬና ሽብሻቦ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ አማኝ በሚያውቀው ቋንቋ፣ በተረዳው እውነትና ባደገበት ባህል ድንቅ በሆነ አብሮነት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ሰው መሆን፣ የማዳኑን እውነት በመግለጥ በልዩ ድምቀት ታከብረዋለች።
ይህ ድንቅ የበረከት ማግኛ ፣የምስክርነት ዐውድና የሕይወት ቃለ ዓዋዲ የሆነው በዓል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ66 አብሕርተ ጥምቀት የተከበረ ሲሆን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊነቱን በጠበቀና በሰላም በመከሩ እጅግ እንዳስደሰታቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ይሄንን ያሉት የቃና ዘገሊላን በዓል ለማክበር በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ባስተላለፉት የበዓሉ ማጠናቀቂያ አባታዊ ቃለ በረከት ነው።
ብፁዕነታቸው ከበዓሉ የተሰበከልን እውነት የክርስቶስ ፍቅሩ፣ ትህትናውና የሰጠን ሰላም በሆኑ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሰላማዊነቱን ጠብቆ በማክበሩ እጅግ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በዚህም በዓል በበረከትና በሰላም እንዲከበር በእጅጉ ያገዙትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመመራሮች፣ የተለያዩ ዘርፎች የጸጥታና የጤና ተቋማትና የውኃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤትና መሰል ተቋማት ላደረጉት ሀገራዊና ታሪካዊ መልካም ሥራ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ በሥርዓትና በሰላም እንዲከበር ግዴታችሁን የተወጣችሁ የሀገረ ስብከትና የየክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ክህናት፣ ያለድካም ማገልገል ያለ ሀኬት መታዘዘን ገንዘብ አድርጋችሁ ያገለገላችሁ ሰንበት ተማሪዎችና የየአካባቢው ወጣቶች፣ ማኅበራት እንዲሁም ምእመናንና ምእመናት በእጅጉ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
“ጥምቀት የድኀነት ለሕይወት ዘለዓለም”
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ