የጻድቁ የአቡነ ሊባኖስ ዘመጣዕ በዓለ ዕረፍት በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ተከበረ

የጻድቁ የአቡነ ሊባኖስ ዘመጣዕ በዓለ ዕረፍት በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ተከበረ።
በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደኖሩ የሚነገርላቸው ጻድቁ አቡነ ሊባኖስ ትውልዳቸው ሮም ሲሆን በግብጽ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ እየተዘዋወሩ በብርቱ ቅዱስን ወንጌል በሕይወት እግዚአብሔርን በእውነት አግልግለዋል።
ጻድቁ አቡነ ሊባኖስ ምንኩስናን ከአባ ጳኩሚስ የተቀበሉ ሲሆን በኢትዮጵያና በኤርትራ የተለያዩ ገዳማትን መሥርተዋል አጽንተዋል።
አቡነ ሊባኖስ በኢትዮጵያ ውስጥ በአክሱምና በሸዋ ግራርያ( ደብረ ሊባኖስ) በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው በሕይወትም በቃልም መንፈሳዊውን ቅዱሱን ተጋድሎ ተጋድለዋል።
የጻድቁ በዓል በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሲከበር ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ ቀኖ የብፀዕነታቸው ልዩ ጸሐፊ፣ መጋቤ ሠናያት የቻለው ለማ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክሆነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊዕ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ጠባይ የገዳሙ አስተዳዳሪ፣ ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰንበተ ተማሪዎች፣ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ ያሬዳዊ ምስጋና በገዳሙ ሊቃውንት እንዲሁም በሰንበት ተማሪዎች ለበዓሉ የተሰናዳዎን የምስጋና ክፍል በወረብ አቅርበዋል።
በመቀጠልም ትምህርተ ወንጌል በሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ ቀኖ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ጸሐፊ የተሰጠ ሲሆን “እግዚአብሔር ቃል የነገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ “(ዕብ.፲፫:፯) በሚል የመጽሐፍ ቃል መነሻነት አስተምረዋል።
በዓሉ በገዳሙ መከበር ከተጀመረ 5 ዓመት መሆኑን የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ ገልጸዋል።
አክለውም በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም የመከበሩ መነሻ ታሪክ ጻድቁ አቡነ ሊባኖስ በገዳሙ የጸለዩበት በምሥረታውም ጉልኅ ታሪካ ያላቸው በመሆኑም እንደሆነ አስታውሰዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለምዳን መምሪያ የጻዱቅ የበረከት በዓል በገዳሙ እንዲከበር ላደረጉ አገልጋዮችንና ምእመናን ምስጋና አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም የቅዱሳን ሕይወት ለእኛ ከትምህርት አልፎ ለበረከትና የሕይወት ዋጋ በመሆኑ በዓላትን ስናከብር በእምነት የምንቀበለውንና የምንባረከውን ሰማያዊ ጸጋ በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በሰጡት ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።