የበዓለ ጥምቀት ዋዜማ ከተራ በዓል በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በተገኙበት ተከብሯል

በየዓመቱ የሚከበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምተቅ ዋዜማ ከተራ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሮእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሰስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱም የሚታሰብበት በመሆኑ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወደ ተዘጋጀው የባሕረ ጥምቀት ቦታ በታሪኩ ምሳሌነት በልዩ የምስጋና ሥርዓት ታጅበው ይጓዛሉ ።
በዚህ መነሻነት በዓሉ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ሲከበር 13 አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት የሚያድሩ ሲሆን በልዩ ሥርዓትና ሰላም ከየመቃድስቱ ወደ ባሕረ ጥምቀት ቦታው ደርሰዋል።
እንደሥርዓቱ አገልግሎቱ የጋራ ቢሆንም የዚህ ዓመት መሪውና ተረኛ አሳዳሪው ደብር የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመሆኑ በሊቃውንቱና በሰንበት ትምሀርት ቤቱ መዘምራን በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ምስጋና በያሬዳው ሥርዐተ ዜማና ሽብሻቦ አቅርበዋል።
በቅድስነታቸው አባታዊ ፈቃድ አጭር መልእክት ያስተላለፉትና ቅዱስነታቸውን የጋበዙት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ የከንባታና አላባ ጠንባሮ አህጉረ ስብከት ጳጳስ እግዘዚአብሔር “እግዚአብሔር ይትናገር ትሑታተ ወይገብር ዐቢያተ” በሚል ርእስ የእግዚአብሔር ከንግግር በላይ የሆነው ፍቅሩንና ቸርነቱን ከኃጢአት በቀር እንደኛ ሰው ሆኖ እንዳከበርን አስተምረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በበኩላቸው ምስጋናውን ያቀረቡትን ሊቃውንቱና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አመስግነው የዋዜማውን በዓል በጸጸሎትና በቡራኬ አጠናቀዋል።
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓለፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ክብራንና ክቡራት እንግዶች ሰንበት ተማሪዎችና በርካታ ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከሚገኙ በጥንታውያትና በታራካውያን አብሕርተ ጥምቀት በመካከል የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ትልቁን ሥፍራ ይይዛል።
“ጥምቀት ለድኅነት ለሕይወት ዘለዓለም”
እንኳን አደረሳችሁ።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ