የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የ 2017 ዓ.ም በዓለ ጥምቀትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት የተሰጠ መግለጫ
“አንሰኬ አጠምቀክሙ በማይ ለንስሐ፣ ወእምድኅሬየሰ ይመጽእ ውእቱ ይጸንዕ እምኔየ፣ ዘኢይደልወኒ እጹር አሣእኖ፣ ውእቱሰ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት፣
እኔ ለንስሐ በውሀ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል”፤ (ማቴ.3:11)
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ምእመናንና ምእመናት ፦
መጋቤ ዓለማት፤ ፈጣሬ ፍጥረታት የሆነው ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረቱ መዳፍ ደግፎ፣ በይቅርታው ብዛት ጠብቆ እንኳን ለ2017 ዓ.ም በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስና ቃና ዘገሊላ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን፣ አደረሳችሁ ።
ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት አስቀድሞ መንገድ ጠራጊ የተባለው የምድረ በዳው ሰባኪ ዮሐንስ መጥምቅ በሁለቱ የኪዳን ሥፍረ ዘመናት መካከል ተገኝቶ ከመላው ይሁዳና ዮርዳኖስ ዙሪያ ወደ እርሡ ለሚመጡት ወገኖች ” …እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፣ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል” እያለ ይሰብክ ነበር ።
ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍለ ምንባብ እንደምንረዳው የጌታን መንገድ የሚያቀና፣ የምድረ በዳው ሰባኪ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በምድረ በዳ በነበረው አገልግሎት በዋናነት የስብከቱ ማዕከል እና ትኩረት ያደረገው ሁለት ሐሳቦችን ላይ ነበር ።
የመጀመሪያው በዓመጻ ሕይወት የምትገኝ ነፍስ ከሚመጣው ቁጣ የምትድንበት ብቸኛ መንገድ ንስሐ ገብቶ በምሕረቱ አደባባይ መቆም መሆኑን መግለፅ ሲሆን “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፣ …ለንስሐ የሚሆን ፍሬም አፍሩ.. እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ” በማለት ንስሐ ማለት የሕይወት ለውጥ ማድረግ፣ ለቀጣዩ ጉዞ ራስን ማዘጋጀት መሆኑን በጭብጥነት ማስተማር ነው ።
ሁለተኛው ትኩረት ደግሞ ከእርሡ በኋላ የሚመጣው ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ የቀደሙት አባቶች ሱባኤ የቆጠሩለት፣በታናሿ ቤተልሔም በኤፍራታ ምድር ሰማያውያንና ምድራውያን በጋራ የዘመሩለት፣ አባቱ በሰማይ ደመና ውስጥ ሆኖ ተወዳጅነቱን የመሰከረለት ፣እግዚአ አጋዕዝት፣ አምላከ አማልክት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማስተዋወቅ ነበር፤ ይኸውም” ከእኔ በኋላ የሚመጣው የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ፤ ነገር ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፣ እርሡ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል በማለት ሲናገር ነው የተደመጠው ።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን እና ምእመናት፦
የባርነት ቀንበራችን የተሰበረበትን፣ የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበትን፣ የነቢያት ትንቢት የተፈመበትን፣ ምሥጢረ ሥላሴ ለሚያምኑት ሁሉ የተገለጠበትን፣ የእግዚአብሔር አብ ድምፅ በሰማይ ደመና የተሰማበትን፣ የጥምቀት ክብረ በዓል ስናከብር የጌታን መንገድ አቅኑ እያለ በምድረበዳ የጮኸውን የንስሐ ድምፅ በማሰብ ያለ ልክ የኖርንበትን ያለፈውን ዘመን ንስሐ በመግባት እንዲሁም የጥምቀት መሥራች እና ምሳሌ የሆነውን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በመለማመድ መሆን ይኖርበታል ።
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አስተምህሮ በአደባባይ ከሚከበሩ ሁለት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል የሀገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት የሚከበረው በዓል እንደተጠበቀ ሆኖ በጠቅላላ ከተማው ከ64 ባላነሱ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሥፍራዎች ይከበራል ።
የስብከት ወንጌል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም በሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል አዘጋጅነትና በሀገረ ስብከቱ ሰ/ት/ቤት አንድነት አስተባባሪነት በ28 የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ሥፍራዎች በዓሉን የተመለከቱ የዳሰሳ ጽሁፍ የሚቀርብ ሲሆን በ64 ቦታዎችም የመምህራን ስምሪት ተደርጓል ።
በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኒስኮ የተመዘገበውን ታላቁን የቤተክርስቲያናችንን በዓል መንፈሳዊ አስተምህሮውንና ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በሰላማዊ መንገድ ለማክበር በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገው በዓሉ አንድ ዓይነት የወንጌል ድምፅ የሚደመጥበት፣ ወጥነት ያለው አገልግሎት የሚሰጥበት እና መነሻና መድረሻው በማዕከል በተሰጠው አቅጣጫ የሚፈጸምበት እንዲሆን የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል ።
በሁሉም የጥምቀተ ባህር ሥፍራዎች ከተሰየሙ የበዓሉ አስተባባሪዎች ጀምሮ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት እና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት አንድነት አመራሮች የተካተቱበትና ተጠሪነቱ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የሆነ በማዕከል ደረጃ አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል ።
የባህረ ጥምቀት ቦታዎች ዝግጁነትን በተመለከተም በአብዛኛው ቦታዎች የመስክ ጉብኝት ተከናውኗል፤ ከይዞታ ጋር ተያይዞ ችግር የነበረባቸውን አንዳንድ ሥፍራዎች ከከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ቦታው ድረስ በመሄድ ችግሩ ዕልባት ተሰጥቶታል፣ የከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከማድረግ ጀምሮ ይዞታዎችን በማስከበር ላደረገልን በጎ ትብብር ከልብ የመነጨ ምሥጋናችንን በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስም እናቀርባለን ።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፦
ሁላችን እንደምንረዳው በፈለገ ዮርዳኖስ በግዘፈ አካል ተገኝቶ የተጠመቀው ጌታ ሰላም ደግሞም የሰላም አለቃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ጥምቀትና ሞት የነበረው የጸብ ግድግዳ ፈርሶ ሰላም ለምድር ሁሉ ስለበዛ በዓሉን ስናከብር ሰላማችንን በመጠበቅ እና የሰላም አየር ለናፈቃቸው ወገኖቻችን በመጸለይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ።
በዓሉ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ የባሕረ ጥምቀቱ የሚሄዱበት፣ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በብዛትና በምልዓት በአደባባይ ወጥተን አምላካችንን በጋራ ዝማሬ የምናመልክበት ከመሆኑም በላይ የበዓሉ ባለቤቶችም እኛው ነንና በጋራ ትብብርና በአንድነት መንፈስ ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ ሥነ ምግባር ማክበር የሁላችን ግዴታ ነው ።
ስለሆነም፦
1.ለበዓሉ የሚመጥን ነጭ ልብስ እና የአገልግሎት ልብስ ከመልበስ ጀምሮ፣ የጋራ ኅብረ ዝማሬ በማቅረብ እና የጉዞ ቅደም ተከተላችንን በመጠበቅ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ማዕከል ያደረገ እና ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጥ አሰላለፍ እንዲኖረን፣
2. ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚደረገው ጉዞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ፤ ከልዕልና ወደ ትህትና መውረዱን የሚያሳይ መንፈሳዊ እሴት ያለበት እንደሆነ የታወቀ በመሆኑ በየትኛውም ጉዞ ዋዛ ፈዛዛ ሳይታይና ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ጋር የሚጣረስ ድርጊት ሳይፈጸም በተቀመጠው አቅጣጫ ብቻ እንዲፈጸም፣
3. የጉዞ ሰዓትን በተመለከተ
– ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም የጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓልን የመነሻ ሰዓቱ እንደዓበያተ ቤተክርስቲያናቱ ርቀት ሆኖ ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚደርሱበት ሰዓት ግን ከ9 – 11 ሰዓት እንዲሆን ።
– የጥር 11 የጥምቀት በዓልና የጥር 12 የቃና ዘገሊላ በዓልን በተመለከተም መነሻ ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ከባሕረ ጥምቀት ተነስተው ሁሉም ታቦታት እንደየርቀታቸው ከ8 – 11 ሰዓት ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ፣ በዚሁ ጉዳይ መንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤትክህነት ጋር በመናበብ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ለተግባራዊነቱም ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችና አስተባባሪ ኮሚቴዎች በጋራ በመቀናጀት ሰዓቱን የማስከበር ሥራ እንዲሰሩ ።
4. አገልግሎታችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የተከተለ መሆን ስለሚገባው አስፈላጊውን ግብዓት ከማቅረብ በቀር ከአበው ካህናት ውጭ በየትኛውም መልኩ በሌሎች አካላት የሚደረግ ማዕጠንት ተገቢነት የሌለው እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመሆኑ እንዳይፈፀም፣ አስተባባሪዎችም ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም በማዕጠንት አገልግሎቱ በካህናት አባቶች በሰፊው እንዲሰጥ ይሁን።
5. በረከተ ጥምቀቱን የማድረስ እና የመርጨት ክንውን የሚፈጸመው በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት በካህናት ብቻ መሆኑ ይታወቃል በዚሁ መሠረት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ባለማወቅ ምክንያት ሥርዓቱ እንዳይፈርስ ወጣት ልጆቻችንም ይህን አውቃችሁ ሥርዓቱን እንድትጠብቁና አገልጋዮች ካህናትም ድርሻችሁን እንድትወጡና ሕዝቡን እንድታገለግሉ እናሳስባለን ።
6. ከልክ ያለፉ እና በተደጋጋሚ የተስተዋሉ ከሥርዓት ውጭ በሆነ መልክ ለታቦታቱ ክብር በማይመጥኑ ሥፍራዎች ላይ እንዲቆሙ የሚደረገው ልምድ እንዲታረምና ሁሉም በሕግና በሥርዓት እንዲመራ።
7. ምእመናን እንደተለመደው ራሳችሁን ከሁከትና አላስፈላጊ ነገሮች በማራቅ በትዕግሥት እና በማስተዋል በዓሉን እንድናከብር እያሳሰብን ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ከሚመለከታቸው ከበዓሉ አስተባባሪዎችና የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተናበበ መልኩ እልባት እንዲሰጣቸው ሊደረግ ይገባል።
በመጨረሻም ፦
በዓለ ጥምቀትን ስናከብር በፍፁም ወንድማዊ ፍቅር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ፤ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትህትና አብነት በማድረግ በመተሳሰብና በመደጋገፍ እንዲሆን እናሳስባለን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ አሜን
ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
አባ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ