የ፳፻፲፯ ዓ/ም በዓለ ልደት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ እንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ተከናወነ

በየዓመቱ የሚከናወነው ይህ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ለቤተ ክርስቲያናችን ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ለሆኑት አባት የሚደረግ ሥርዐት ነው።
መርሐ ግብሩ ከበዓለ ልደት በተጨማሪ በበዓለ ትንሣኤ እንዲሁም በዘመን መለወጫ የሚካሔድ ነው።
በዚህ በ፳፻፲፯ ዓ/ም በዓለ ልደት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ዛሬ ጥረ ፩/፳፻፲፯ ዓ/ም በመንበረ ፓትርያርክ ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞችእና የጋሞ ማኅበረሰብ ኦርቶዶክሳውያን ተገኝተዋል።
መርሐ ግብሩ በቅዱስነታቸው መሪነት በመንበረ ፓትርያርክ የካህናት አስተዳደር መምሪያ አስተባባሪነት በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጸሎተ ወንጌል የደረሰ ሲሆን በቅዱስ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ደቀ ደቀመዛሙርትና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማእከላውያን መዘምራን እንዲሁም በጋሞ ማኅበረሰብ መዝሙርና ወረብ ቀረቧል።
በመቀጠልም በሁለት መምህራን ቅኔያት ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አሰተዳሪዎች ለቅዱሰነታቸው የእንኳን አደረሰዎ መልእክት አስተላልፈዋል።
ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ መንበረ ፓትርያርክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ወክለው ለቅዱስነታቸው የእንኳን አደረሰዎ መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በተደረገው መርሐ ግብር አመስግነው በዓልን ለማክበር ሰላም ሲኖር ነውና ለሀገራችን ሰላም በመጸለይና በተግባር በማሳየት መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
በዓለ ልደቱ ለሁሉም ፍጥረት ሰላም እና ዕረፍት የታወጀበት በመሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቶስ የሰጠንን እውነተኛ ሰላም መልእክተኞች ከመሆን አልፈን ለተግባሩ አርአያ በመሆን ትውልድ እንዲያርፍ ሀገር ሰላም እንድትሆን መሥራት አለብን ብለዋል።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ