የመካነ መቃብራት አያያዝና አጠቃቀም ትኩረት እንደሚሹ ተገለጸ።

የሰው ልጆች ምድራዊ ቆይታችንን አጠናቀን ከዚህ ዓለም በሞት በምንለይበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን አስከሬናችንን ተቀብላ በክብር በቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ ውስጥ ታሳርፈዋለች። በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ መካነ መቃብራት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን ይዘው የሚገኙ ቢሆንም በተደጋጋሚ ጊዜ ከምእመናን ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል ለቦታው ልዩ ትኩረት ካለመስጠት የተነሳ የፅዳት ችግር እና የተለያዩ አላስፈላጊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው መሆኑ ይገኛል።
ስማቸውን እና ቦታው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል እንደገለጹ በደብራቸው የሚገኙ አገልጋዮች እና ምእመናን የመካነ መቃብሩ ስፍራ በአግባቡ ካለመያዙ የተነሳ ፅዳጅ ማስወገጃ እየሆነ እንዳለ የገለጹ ሲሆን አክለውም ቦታው ግልፅ ያልሆነ ነው በዛ ምክንያት የሱሰኞች መዋያ እንዲሁም የሌቦች መደበቂያ በመሆኑ ለደህንነታችን እየሰጋን እንገኛለን የሚመለከታቸው አካላት ለሕንፃ ቤተክርስቲያኑ እና ለቅፅር ግቢው የሚሰጡትን ትኩረት ለመካነ መቃብሩም መሰጠት እንዳለበት ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።
ተሚማ እንደዘገበው በጥሩ ሁኔታ ተይዘው ከሚገኙ መካነ መቃብራት መካከል አንዱ የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴደራል መሆኑን በጉብኝቱ አስታውሷል። “ቦታው ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ አገልግሎት አቁመን ወደ ሌላ አድባራት ምእመናን እንዲሄዱ ተደርጎ ነበር” በማለት የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ኪሮስ ጸጋዬ የነበሩትን ችግሮች የገለጹ ሲሆን ካቴድራሉ ቀደምት የነበረበትን ሁኔታ እና አሁን ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆን የተደረገበትን ሂደት ሲያስረዱ “ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ለቦታው ልዩ ትኩረት በመስጠት እና በታቀደ መልኩ በመስራት አሁን ያለበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ችለናል” ብለዋል።
ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ኪሮስ ጸጋዬ አክለውም “አቅም ለሌላቸው ምእመናን የነፃ አገልግሎት እስከመስጠት የደረስንበት ሁኔታ አለ” ያሉ ሲሆን “ዋናው ፍላጎታችን ለትርፍ ሳይሆን ምእመናን በአግባቡ እንዲገለገሉ ነው ፤ ምእመናንም ይህንን መረዳት መቻል አለባቸው” ብለዋል።
በመጨረሻም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚስተዋለውን የመካነ መቃብራት አያያዝ ጉድለትን በተመለከተ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ኪሮስ ጸጋዬ “ነገሮች ሁሉ በእቅድ እና በተጠና መንገድ መሆን አለበት ፤ ያሉንን ቦታዎች በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ለምእመናን ምቹ የሆነ አገልግሎት መስጠት ስለማንችል በዋናነት ከሌሎች ልማቶች እኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል።
ተሚማ