“ሰላም ከአንገት በላይና ዝም ላለማለት ያህል የምንናገረው ሳይሆን ዋጋ ከፍለን የምናመጣው ነው”

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ
ጥቅምት ፳፭/፳፻፲፯ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሰላም ሚኒስቴር ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም “ሰላም ከአንገት በላይና ዝም ላለማለት ያህል የምንናገረው ሳይሆን ዋጋ ከፍለን የምናመጣው ነው ብለዋል።
የቅዱስነታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ሰላምየ አኀድግ ለክሙ ወሰላመ አቡየ እሁበክሙ፡- ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፡፡” ዮሐ. ፲፬፥ ፳፯
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በሚታይ ሰውነት የተገለጠው ሰላምን ለማምጣት ነው፡፡ የማዳን ተግባሩን አከናውኖ፤ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አድርጎ ባረገ ጊዜም ዓለም እንደምትሰጠው ሰላም ያይደለ ልቡናን የሚያሳርፍ፣ መንፈስን የሚያረጋጋ እውነተኛ ሰላምን ሰጥቶናል፡፡ ልዑል አምላክ ትሑት ሥጋን በመዋሐዱም ታላላቆች ለይቅርታ ዝቅ በማለት የሰላም ምክንያት መሆን እንደሚችሉ በተግባር አስተምሮናል።
ሰላም የሰው ልጆች ፍላጎት፣ የብዙ ምንዱባን የየዕለት ናፍቆት ነው። የበርካታ ዘመናት ቅርሶች፤ ጊዜ፣ ገንዘብ እና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው ግንባታዎች በሰላም ማጣት በቅጽበት ይፈርሳሉ። ሰላም ካለ የዓለም ሀብት ለሁሉም በቂ ነው። ሰላም ማጣት ግን ብዙ ሠራዊት፣ ብዙ የጦር መሳሪያ እንዲዘጋጅ እያደረገ ሀብትን ያወድማል። ጦርነት ማለት ሀብትና ሕይወትን ወደሚነድ እሳት ውስጥ መጣል ነው። የአንደኛና የሁለተኛ ዓለም ጦርነት፣ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ጠባሳው አሁንም የዓለምን መልክ አበላሽቶታል። ሰላም በውስጥዋ ገራምነት፣ ትዕግሥት፣ ታዛዥነትና በትህትና ዝቅ ማለት ስለሚገኙ መራራ ትመስላለች፤ በውጤቷ ግን ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከመከራ ማትረፍ የሚቻል በመሆኑ ዋጋዋ ከፍ ያለ ነው።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም የሆነው ክርስቶስ የሚሰበክባት፣ የሰላም መልእክተኞች በውስጥዋ የሚመላለሱባት፣ በግብረ ኃጢአት የወደቁት በንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቁባት የሰላም ድልድይ ስለሆነች በሥርዓተ ቅዳሴዋ ሰላምን ደጋግማ ታውጃለች፤ በጸሎቷ ለመላው ዓለም ሰላምን ትለምናለች፤ በጉልላትዋ ላይ የሰቀለችው መስቀልም ሰላምን የሚሰብክ ነው፤ የመስቀሉ ቅርፅ ወደ ላይና ወደ ጎን መሆኑም ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ሰላም መሆን እንዳለብን የሚያስገነዝበን ነው። ታሪካችን እንደሚነግረን ወንድማማቾች ሲጋደሉ፣ በሕዝብ መካከል መተላለቅ ሲመጣ ቤተ ክርስቲያን ታቦት አክብራ፣ በእሳት መካከል ገብታ ሰላምን ስታወርድ የኖረች ናት። በሀገር ውስጥ ግጭቶች በተፈጠሩበት ጊዜም የሰላም ጥሪን ያላስተላለፈችበት ቀንና ሰዓት አይገኝም፡፡
ሰላምን የመወያያ ርእስ አድርገን ስንሰባስብ በጦርነት መካከል የተጨነቁ ሕዝቦች፣ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እና ምን እየተደረገ እንዳለ በውል የማይገነዘቡ ደካሞች ተስፋ ያደርጉናል። ስለዚህ ሰላም ከአንገት በላይና ዝም ላለማለት ያህል የምንናገረው ሳይሆን ዋጋ ከፍለን የምናመጣው ስለሆነ ይህ ጉባኤ ከውይይት ባሻገር በተግባር ጭምር የሰላም ተምሳሌት መሆን እንደሚገባው ለማሳሰብ እንወዳለን።
ዓለም በዚህ ወቅት አስጊ በሆኑ ጦርነቶች ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ በሩሲያና በዩክሬን ያለው ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ አናግቷል፤ ከሁሉ በላይም ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት እየቀጠፈ ነው። በእስራኤል፣ በፍልስጤም እና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ያለው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚነካ ነውና በጦርነቱ የሚሳተፉት በሙሉ ወደ ሰላም እንዲመለሱ፤ የዓለም መሪዎችም ልበ ሰፊ ሆነው ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን ውስጥ ያሉት ግጭቶች የመቆሚያ ድንበራቸውን ያገኙ ዘንድ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር የተባረከ ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፳፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
©የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ/ጽ/ቤት፤