በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ሰባክያነ ወንጌል በወንጌል አገልግሎቱ ዙሪያ በቀጣይ ሳምንት ሰኞና ረቡዕ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰባክያነ ወንጌል በወንጌል አገልግሎቱ ዙሪያ ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን እና ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ/ም በየክፍላተ ከተሞቻቸው ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል የተጣለበትን አደራ ለመወጣት እና በወንጌል አገልግሎቱ ዙሪያ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ባሉ ገዳማትና አድባራት ተመድበው የሚሠሩ ሰባክያነ ወንጌልን ከማንቃት፣ ግንዛቤ ከመፍጠር፣ ከማደራጀት እና አቅምን ከማሳደግ አኳያ ሰፊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።
በዚህም መሠረት የዚሁ አካል የሆነ የግንዛቤ ማስጨባጫ መድረክ ሰባቱን ክፍላተ ከተሞች ለሁለት በመክፈል የፊታችን ሰኞ እና ረቡዕ በየክፍላተ ከተሞቻቸው ውይይት ለማድረግ ታስቧል። በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት በመጀመሪያው ዙር ማለትም፡-
ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ ም
1. አራዳ እና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ
ወንጌል አዳራሽ፤
2. አዲስ ከተማ፣ ልደታ እና ቂርቆስ
ክፍላተ ከተማ በሜክሲኮ ማሕደረ
ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም
ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል
አዳራሽ
3. የካ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተሞች
በየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል
ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል
አዳራሽ ውይይታቸውን የሚያደርጉ
ይሆናል።
– ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ ም
1. ኮሌፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በቀራንዮ
መድኃኔዓለም የስብከተ ወንጌል
አዳራሽ
2. ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ
በብሥራተ ገብርኤል ስብከተ ወንጌል
አዳራሽ
3. አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ
በቃሊቲ መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል
ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል
አዳራሽ።
4. ቦሌ ክፍለ ከተማ
ውይይታቸውን ያደርጋሉ።
በውይይታቸውም ተግባራዊ ኅብረት ለወንጌል አገልግሎት በሚል ርዕስ ውይይት እንደሚያደርጉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ዋና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አብነት ዐሥራት ገልጸውልናል። በተጨማሪም በዚህ ዘመን በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ላለችው ቤተክርስቲያን ብቸኛው መፍትሔ ወንጌል እና አንድነት መሆኑን ሁሉም አገልጋይ ተረድቶት መምህራነ ወንጌል ለዚህም መፍትሔ መሆን እንደሚችሉ እና የቤተክርስቲያኒቱ ዋና ዓላማ ወንጌልን መስበክ እና ያላመኑትን ማሳመን የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን ተገንዝበው ሁሉም አገልጋይ በዓላማ እንዲሠራ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይታመናል።
በዕለቱም ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ/ም በሀገረ ስብከት ደረጃ የተመሠረተው የሰባክያነ ወንጌል ኅብረት በየክፍላተ ከተማው መዋቅሩን በመዘርጋት የክፍለ ከተማ የሰባክያነ ወንጌል ኅብረት የንዑሳን ኮሚቴዎች ምርጫ እንደሚያደርግ እና ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ ም በቦሌ ደ/ሳሌም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ስለሚያከናውነው የእውቅና እና የምስጋና መርሐግብር ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥም ታውቋል።
በተጠቀሱት ቀናት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ያላችሁ የገዳማትና አድባራት ሰባክያነ ወንጌል በሙሉ በየክፍለ ከተሞቻችሁ በመገኘት የነቃ ተሳትፎ እንድታደርጉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ጥሪውን ያስተላልፋል።
ዘገባውን ላከልን የኅብረቱ መረጃ ክፍለ ነው።