የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መከበሩን አስመልክቶ የምስጋና መልእክት አስተላለፈ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በመከበሩ የምስጋና መልእክት አስተላለፈ።
የ፳፻፲፯ ዓ/ም የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል ዐደባባይ ቅዱስ ፓትርያርካችን፣ ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት፤ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሚኒስትሮች፣ የአሜሪካን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በሰላም ተከብሯል።
የደመራ በዓል በተጨማሪ በ፪፻፶፩ዱም የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት በሰላም የተከናወነ ሲሆን ህዝበ ክርስቲያኑ ተቀራርቦ በሚኖርባቸው አደባባዮችና ሰፈሮች ውስጥ ከ፪ሺህ ፫ መቶ በላይ ደመራዎች ተደምረው ያለምንም የጸጥታ ችግርና ጉዳት ተጠናቋል።
በመስቀል አደባባይ በተከበረው የደመራ በዓል ከ፪ሺህ ፭መቶ በላይ ሰንበት ተማሪዎች፤ ፬መቶ ሊቃውንት መንፈሳዊ አገልግሎት በቀጥታ የሰጡ ሲሆን ፪ሺህ ፭መቶ ካህናት ልብሰ ተክህኖ በመልበስ ፮መቶ ወጣቶች ደግም ከፀጥታ አካላት በመተባበር ሥርዓት በማስከበር ተሳትፈዋል።
በዓሉ ሰላማዊ እና መንፈሳዊ ሆኖ እንዲከበር የመንግሥት የፀጥታ አካላት ለወራት የተዘጋጁ ሲሆን ከቤተክርስቲያናችን አካላት ጋር በመተባበር የተጫወቱት ሚና የማይተካ የነበረውን ጫና እና ምቹ ያልሆነ የእየር ሁኔታን በመቋቋም የተወጡት በመሆኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።
በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ፤የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በዓሉን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ ያደረጉት ዝግጅት የቅርብ ክትትልና ጥረት በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ያስቻለን በመሆኑ በመላው ህዝበ ክርስቲያንና አገልጋዮች ስም ሀገረ ስብከቱ ምስጋናውን ያቀርባል።
መላው ህዝበ ክርስቲያንም የበዓሉ ባለቤት መሆኑን በመረዳት ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ፍጹም ሰላማዊ በዓል ሆኖ እንዲያልፍ ማድረግ በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን ማለትን ይወዳል።
የፌዴራል ፖሊስ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ፤ የትራፊክ ፖሊስ እና ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላትም በዓሉ የተሳካ ሰላማዊ እንዲሆን የደከማችሁት ድካም ውጤታማ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በሀገረ ስብከታች እና በመላው ህዝበ ክርስቲያናችን ስም ጽ/ቤቱ ምስጋናውን ያቀርባል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
መስከረም ፲፯/፳፻፲፯ ዓ/ም