ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል በከፍተኛ ድምቀትና ሰላም መከበሩን አስመልክቶ የምስጋና መልዕክት አስተላለፈች።
የ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓትና ድምቀት ተከብሮ በመዋሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።
በዓሉ በተዋበና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ዝናብና ቁር ሳይበግረው በጽናትና ፍጹም በሆነ መንፈሳዊነት በዓሉን ማክበሩ እጆግ የሚያስደንቅ ሲሆን መርሐ ግብሩ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችል ተረኛው ደብር፣ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ልጆቻችንና በበዓሉ ላይ ልዩልዩ መንፈሳዊ ትርኢት ስታቀርቡ የነበራችሁ በሙሉ ላሳያችሁት ጨዋነት የተሞላው መታዘዝ ቅድስት ቤተኮርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
ሕዝበ ክርስቲያንኑ በዓሉ ወደ ሚከበርበት መስቀል አደባባይ በሚጓዝበት ወቅት ፍጹም ጨዋነትና መንፈሳዊነትን በተላበሰ መልኩ ለመንግስት የጸጥታ አካላት ትብብር በማድረግ፣ራሱም ጸጥታ አስከባሪና ተባባሪ በመሆን ያሳየው ድንቅ ትብብርም የሚደነቅ ሲሆን በዓሉን ከሚያውኩ ተግባራት በማራቅም ቤተክርስቲያን ከበዓሉ አስቀድማ ያስተላለፈቻቸውን የጥንቃቄ መልዕክታት በሚገባ በመፈጸም ታዛዥነቱን በማስመስከሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።
በሌላ በኩል በዓላችን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የፌዴራልና የክልል የደህንነት፣የፓሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሙያዊ ግዴታችሁን በሚገባ በመወጣት ያደረጋችሁት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ስታቀርብላችሁ በከፍተኛ ደስታ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዓሉ እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ እንዲከበር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማለትም የስቴጅ፣የክብር እንግዶች ወንበር፣አካባቢውን የማስዋብ ሥራና የድምጽ ማጉያዎችን ወጪ በመሸፈን እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሁሉ በፍጥነትና በቅንነት ምላሽ በመስጠት ላደረገልን ትብብር እያመሰገነች በተለይም ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀልጣፋ አመራር በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች ።ይህ አይነቱ መተጋገዝና የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራት ልምዳችንም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ትወዳለች።
በሌላ በኩል በዓሉ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ በጠቅላይ ቤተክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁት ዐበይትና ንዑሳን ኮሚቴዎችም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር በጥምረት የሰራችሁት ስራዎች እጅግ ውጤታማና ስኬታማ በመሆናቸው እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ትወዳለች።
በአጠቃላይ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓላችን በተዋበ፣በተሳካና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ላደረጋችሁልን ተቋማት በሙሉ በተለይም በዓላችን ፍጹም መንፈሳዊ በዓል መሆኑን በዓለም መድረክ በማሳየት ደረጃ ዝናብና ቁር ሳይበግራችሁ በጽናት በመቆም በዓላችሁን በሚገባ ላከበራችሁ ኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን አደረሳች፤ በዓለ መስቀሉ የሰላም፣የደስታና የፍቅር በዓል ይሁንላችሁ በማለት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መልካም ምኞቷን ትገልጻለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ