“#የመስቀሉ ቃል ማለት እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ለእርሱም ታዘዙና ተገዙ ማለት ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“እስመ ነገረ መስቀሉሰ ዕበድ ውእቱ በኀበ ኅጉላን ወበኀቤነሰ ለእለ ድኅነ ኃይለ እግዚአብሔር ውእቱ፤ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፤ ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው”(1ቆሮ. 1÷08)፤
በመስቀሉ ኃይል ከፍዳ ኃጢአት ያዳነን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመተ ምሕረት በዓለ ቅዱስ መስቀል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
ጌታችን በዚህ ዓለም በተገለጸበት ዘመን የግሪካውያን ፍልስፍና ሰፊ ስፍራ አግኝቶ በመካከለኛው ምሥራቅ በሰሜን አፍሪካና በአውሮፓ የተስፋፋበት ዘመን ነበር፤ የግሪካውያን ባህልና ፍልስፍና የተመሠረተው በግዙፉ ቁስ ላይ እንደመሆኑ በግዙፉ መሳሪያ ላይ የሚተማመን ነበረ፤ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ሥር ሰዶ በነበረበት ጊዜ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊ ኃይል በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ ጌታችን በሰው መካከል ተገኝቶ አጋንንትን ወደ ጥልቁ ሲያሰምጥ፣ ልዩ ልዩ በሽታና ደዌ ያላቸውን ሲያድን፣ ሙታንን ሲያነሣ፣ ብዙ ተአምራትንና አስደናቂ ነገሮችን ሲያሳይ በመንፈሳዊ ኃይል እንጂ በቁሳዊ ኃይል አልነበረም፤ በመሆኑም በወቅቱ በዓለም ውስጥ ቁሳዊ ኃይልና መንፈሳዊ ኃይል ተብለው የሚታወቁ እነዚህ ሁለት ኃይላት እርስ በርስ ይጋጩ ነበር፤ ዓለም በቁሳዊ ኃይል ተማምኖ በጉልበት የሚያደቀውን በመሳሪያ የሚቀጠቅጠውን ሲሻ፣ መንፈሳዊው ኃይል ደግሞ ከቊሳዊ ኃይል በላይ የሆነውን መለኮታዊ ኃይል በመጠቀም የሰውን ሁለንተና ሕይወት ለማዳን ይሰራ ነበር፤
እነዚህ ኃይሎች ከሥር መሠረቱ አነሣሣቸው፣ አመጣጣቸውና የኋላ ጀርባቸው የተለያየ በመሆኑ የሚጣጣሙ አልነበሩም፤ በዚህ ዓለም ጥበብ ወይም ፍልስፍና የሚተማመኑቱ ግሪካውያን የመስቀሉን ቃል ሲሰሙ እንደ ሞኝነትም እንደ ድክመትም አድርገው ይመለከቱ ነበር፤ ወልደ እግዚአብሔር በሥጋ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ በለበሰው ሥጋም በኛ ፈንታ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ ሞተ፤ በሞቱም እኛን ከረቂቁ ፍዳ ኃጢአት አዳነን የሚለውን የመስቀሉ ቃል ወይም አስተምህሮ ቁሳውያን እንደሞኝነትም እንደ ደካማነትም በመመልከታቸው ለጊዜውም ቢሆን የመስቀሉ ቃል ጠጥሮአቸዋል፡፡
ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስቀሉ ቃል ሞኝነት መስሎ ለሚታያቸው የመጨረሻ ዕድላቸው መጥፋት ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመስቀሉ ቃል ሰውን ለማዳን የተደረገ የእግዚብሔር ኃይል እንደሆነ አምነው ለሚቀበሉና ለሚኖሩበት የመጨረሻ ዕድላቸው መዳን ነው በማለት የሁለቱም ዕድል አነጻጽሮ ይገልጻል፤ የቊሳውያን ግንዛቤ በቊሳዊው ዓለም የተገደበ ስለሆነ ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚያውቁት ባለመኖሩና ለማወቅም ተነሳሽነቱ በማነሱ፣ በሌላም በኩል መንፈሳውያኑ ደግሞ ከቊሳዊው ዓለም ባለፈ መንፈሳዊው ዓለም መኖሩና ዘላቂና ወሳኝ ኃይልም ያለው መንፈሳዊው ዘንድ ነው ስለሆነም ሰው በቊሳዊ ኃይል ሳይሆን በመንፈሳዊ ኃይል ዘላቂ ድኅነትን ያገኛል ብለው በማስተማራቸው ልዩነቱ ተፈጥሮአል፤ ከዚህ አንጻር የችግሩ ዋና ማጠንጠኛ የመንፈሳዊው ኃይል መኖርና አለመኖር ማወቅ ወይም ማመንና አለማመን ነበረ፤ ይህ እሳቤ ዛሬም ሳይቀር የዓለምን እሳቤ እንደሰነጠቀ ነው፤
ይሁን እንጂ በንጹህ ኅሊና በቅን ሰብእና እንደዚሁም በጥልቅ አእምሮ ለሚያስተውለው ሰው፣ ሓቁ ብዙም የራቀና የረቀቀ አይደለም፤ ምክንያቱም ዓለም እየተመራ ያለው በሚታየው ግዙፍና ደካማ ቊስ ሳይሆን በማይታየውና በረቂቁ መንፈሳዊ ኃይል እንደሆነ ሥነ ፍጥረት ይመሰክራልና ነው፤ በዓለማችን ለሚከናወኑት ቊሳዊና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሙሉ መልስ ያለው መንፈሳዊው ኃይል እንጂ ቊሳዊው ኃይል አይደለም፤ እንዳልሆነም ኅሊናችን ይመሰክርልናል፡፡ ዛሬ በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ በዓል የምናከብረው የቅዱስ መስቀል በዓልም ከዚህ በላይ የጠቀስነው የሁለቱ አካላት ግጭት የፈጠረው ክሥተት ነው፤ መንፈሳዊው ሰው ከመስቀሉ በቀር ከፍዳ ኃጢአት እድንበታለሁ የምለው ሌላ ትምክህት የለኝም ብሎ የመስቀሉን ዘላቂ አዳኝነትን ከፍ አድርጎ ሲዘምር፣ ቊሳዊው ኃይል አልተመቸውም፤ ዝም ብሎ ማየትም ምርጫው አልነበረም፤ ስለሆነም ባለው ዓቅም ሁሉ ተንቀሳቅሶ መስቀሉን ከገጸ ምድር በማስወገድ በእሱ ላይ የተመሠረተውን አስተምህሮና እምነት እንዳይነሣም እንዳይወሳም በማሰብ መስቀሉን ቀበረ፤ ቊሳውያን መስቀሉን ቢቀብሩትም የመስቀሉን ቃል ሊቀብሩ አልቻሉም፤
ምክንያቱም የመስቀሉ ቃል ቊሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፣ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ፣ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፣ ሰብአዊ ሳይሆን መለኮታዊ፣ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ነውና፤ ይህም በመሆኑ ቊሳዊ የሆነው ዕፀ መስቀል ቢቀበርም እሱ የተሸከመው ቃለ ድኅነት በረቂቁ የሰው አእምሮ ተቀርጾና ተዘግቦ ስለሚኖር ተቀብሮ ሊቀር አልቻለም፤ በሂደትም ያልተቀበረው የመስቀሉ ቃለ ድኅነት በንግሥት ዕሌኒ አእምሮ ውስጥ የእምነት ኃይል አቀጣጥሎ የተቀበረውን ዕፀ መስቀል በዛሬው ዕለት ከጥልቅ ጉድጓድ አውጥቶአል፤ በዚህም አሸናፊነቱን አረጋግጦአል፤ ዛሬ የምናከብረው በዓልም ይኸው ኃይለ እግዚአብሔር ለማሰብና በሱ ያለንን እምነት ለማስጠበቅና ቃለ ድኅነቱን ለማሥረጽ ነው፤ መስቀል ኃያልና አሸናፊ ቢሆንም ረቂቁንም ሆነ ግዙፉን ጠላት የሚያሸንፈው በሐቅና በሰላም፣ ኅሊናን በመርታትና በማሳመን እንጂ እንደ ቊሳዊ ኃይል አይደለምና እነሆ ዕፀ መስቀሉ በዛሬው ዕለት በኃይለ እግዚአብሔር በታጀበ ጢሰ-ዕጣን ከተቀበረበት ጉድጓድ በሰላም ሊወጣ ችሎአል፡፡
የመስቀሉ ቃል ዛሬም ተቃራኒ ኃይል አላጣም፤ ዛሬም ለመስቀሉ ቃል ጀርባቸውን የሚሰጡ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ ስጋቱ ጭንቀቱ ግጭቱ አለመተማመኑ በዓለማችን ከምን ጊዜውም በላይ ተንሰራፍቶአል፤ ሀገራችንም ከዚህ የተለየች ልትሆን አልቻለችም፤ በዓለ መስቀሉን ከማንኛውም ክፍለ ዓለም በተለየ ሥነ ሥርዓት ብናከብርም የመስቀሉ ሰላም ግን በሀገራችንና በሕዝባችን እየተነበበ አይደለም፤ ይህንን ለማስገንዘብ የሚተላለፈው መልእክትም እየተደመጠ አይመስልም፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው የተሟላ ደኅንነት ያግኙ ማለት ነው፤ የመስቀሉ ቃል ማለት የሰዎች ሃይማኖታዊ ነጻነት ይከበር፤ በሕይወት የመኖር ሰብአዊ መብታቸውም ይጠበቅ ማለት ነው፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በዚች ምድር በእኩልነት በአንድነት በመተጋገዝ በመረዳዳት በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሰላም በፍቅር በስምምነት በመተባበር ይኑሩ ማለት ነው፤
የመስቀሉ ቃል ማለት የሰው ሕይወት በዚህ ዓለም የተገደበ አይደለም ዘላለማዊ በሆነው መንፈሳዊ ዓለምም ሕይወት በቀዋሚነት ይቀጥላልና እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ለእርሱም ታዘዙና ተገዙ ማለት ነው፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም የመዳን ዕድል ተከፍቶላችኋልና በደሙ ታጥባችሁ ወደ እግዚብሔር መንግሥት ግቡ ማለት ነው፤ ይህንን የመስቀል ቃል ዓለም ብትቀበለው ኖሮ በየጊዜው እያንዣበባት ያለው ስጋት ሁሉ ቦታ አይኖረውም ነበር፤ አሁንም በመስቀሉ ስም ለዓለም ሕዝብም ሆነ ለሀገራችን ዜጎች ሁሉ የምናስተላልፈው ዓቢይ መልእክት የመስቀሉ ቃል ሁላችንንም በእኩልነትና በፍቅር የሚያስተናግድ ነውና እሱን እንቀበል፤ የዓለም ስጋቶች በሙሉ ሊቀረፉ የሚችሉ በመስቀሉ ቃል ብቻ ነውና የሚል ነው፡፡
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ በዓል ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!! አሜን::
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ
ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 16 ቀን 2017ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ