የቤተክርስቲያን ተወካዮች በግብፁ ጉባኤ ላይ ያልተገኙት በግል በገጠማቸው እክል ምክንያት መሆኑን የውጭ ግንኙነቱ መምሪያ አስታወቀ።

መስከረም 6 እና 7/2017 ዓመተ ምሕረት በግብፅ አል ናትሩ አባ ቢሾይ ገዳም በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተናጋጅነት በተካሄደው የአኃት እና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ያልተገኙት በግል በገጠማቸው እክል ምክንያት ሲሆን ተተኪ ልዑክ ለመላክ እስከ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓመተ ምሕረት ድረስ የተደረገው ጥረት ቪዛን ጨምሮ አስፈላጊውን የጉዞ ሰነዶች ለማሟላት ከሚያስፈልገው ጊዜ ያጠረ በመሆኑ ሊሳካ አልቻለም።

ከብፁዕ ወቅዱስ ታዎድሮስ 2ኛ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በተጻፈ ደብዳቤ የተጋበዘችው ቤተ ክርስተያናችንዶች የግብዣ ጥሪው እንደደረሳት ከመርሐ ግብሩ ሁለት ወራት አስቀድሞ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አመራር ሰጪነት በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 5 በተደነገገው መሠረት በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የበላይ ሓላፊ እና የምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ እንዲሁም ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል ግርማ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ ፕሬዚዳንት ቤተክርስቲያናችንን ወክለው እንዲገኙ ተመድበው የነበረ ቢሆንም ልዑካኑ በገጠማቸው እክል ምክንያት በጊዜው ሊገኙ እንዳልቻሉ ከውጭ ግንኙነት መምሪያ ባገኘነው መረጃ ለማረጋገጥ ችለናል ሲል የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዘግቧል።