የማ/ስ/ቅ/ ልደታ ለማርያምና ደ/መ/ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን (Lideta-EPMS) የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ (Software) አበልጽጎ አስመረቀ!!
በአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ የIct ባለሙያዎች የተዘጋጀው የሠራተኞች እና የምዕመናን አጠቃላይ መረጃ መመዝገቢያ እና ማስተዳደሪያ Lideta Employee & Parishioners Management System (Lideta-EPMS) የተሰኘ ሶፍትዌር አበልጽጎ በዛሬው ዕለት አስመረቀ።
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲና የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሶፍትዌሩን በይፋ መርቀው አስጀምረዋል።
መ/ር ዮሐንስ እሸቱ የደብሩ የICT ባለሙያ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና ቴክኖሎጂ” በሚል ስያሜ የተዘጋጀውን የደብሩን የሶፍትዌር አሠራር አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቤተክርስቲያን የቴክኖሎጂ ምንጭ እንደሆነችና ለዓለምም ቴክኖሎጂን ያበረከተች መሆኗን ገልጸው ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለምን ክፍተት ተፈጠረ የሚለውንም ጥያቄ አንስተው አብራርተዋል።
የቤ/ክ ነባር የአስተዳደር ሥራዎች የሚከናወኑት ማኑዋል በሆነ መንገድ ማለትም በወረቀት ላይ የተደገፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መረጃን በወረቀት ብቻ መያዝ ደግሞ ለሰዓትና ለንብረት ብክነት እንደሚዳርግ አውስተዋል፣ በተጨማሪም ደካማ የሆነ የመረጃ አያያዝ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።
ስለሆነም በሲስተም የተደገፈ የመረጃ አያያዝን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ይህም ደግሞ የሰዓትና የንብረት ብክነትን ይቀንሳል ፤ መረጃም በቀላሉ እንዲገኝና እንዳይጠፋ ይረዳል ሲሉ ጠቅሰዋል።
በደብሩ የተዘጋጀው የሶፍትዌር ዝግጅት ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን አንደኛው የሠራተኞች መረጃ ሲስተም እና ሁለተኛው የምእመናን መረጃ ሲስተም እንደሆነ ገልጸዋል።
በምእመናን የመረጃ አያያዝ ሲስተም ውስጥ የሰበካ ጉባኤ አባልነት መረጃ፣ የጥምቀት መረጃ፣ የጋብቻ መረጃ ፣ የሞት መረጃ መካተታቸውን አብራርተዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መ/ገ ሀብተወልድ ተገኝ በደብሩ የተሠሩትን ሥራዎችና ሊሠሩ የታቀዱትን በሪፖርት መልኩ አቅርበዋል።
በሪፓርታቸውም በደብሩ 217 አገልጋይ ሠራተኞች እና 52,954 ምእመናን እንዳሉ ገልጸዋል፣ሊሠሩ የታሰቡትን ዕቅዶች አስመልክተው የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ በሚል ከፋፍለው አቅርበዋል።
ከጥንት ጀምሮ ለደብሩ እድገት መልካም አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት በሙሉ የሽልማትና የሰርተፊኬት ምስክር ተበርክቷል።
ሊ/ጉ ቆሞስ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ “በእኔ እመኑ በሥራዬም እመኑ” ብሎ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል መነሻ አድርገው መልእክት አስተላልፈዋል።
የቤተክርስቲያን ዋና አገልግሎት ነፍሳትን ማዳን እንደሆነ ጠቅሰው ዘመኑ ያመጣቸውን ጠቃሚ የሆኑትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የቤ/ክ አገልግሎትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ክቡር ሥራ አስኪያጁ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ “( ሮሜ 12፥11) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል መነሻ በማድረግ ተግቶ መሥራት እንደሚገባ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በዘመናዊ አሠራር በተለይ ደግሞ በሶፍትዌር ሲስተም መረጃዎችን ሰንዳ ለምእመኖቿ ቀልጣፋ አገልግሎት እንድትሰጥ ሁሉም የቤተክርስቲያን አካል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በደብሩ የተዘጋጀው የሠራተኞች እና የምዕመናን አጠቃላይ መረጃ መመዝገቢያና ማስተዳደሪያ ሶፍትዌር እጅግ የሚያስደስትና ለሌሎች አድባራትና ገዳማት ትልቅ ምሳሌ መሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል።
ብፁዕነታቸው የደብሩን ሰበካ ጉባኤ፣ የአስተዳደር ሠራተኞችን፣አገልጋይ ካህናትንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለመልካም ሥራዎቻቸው አመስግነዋል።
በ2013 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው የደብሩ አይሲት ክፍል በ8 ወራት ጊዜ ውስጥ Lideta Employee & Parishioners Management System (LEPMS) የተሰኘ መተግበሪያ አበልጽጎ ለሥራ ዝግጁ ማድረጉንና የሰበካ ጉባኤ አባልነት ፣ የመዝገበ ሙታን ፣ የመዝገበ ጥምቀትና የመዝገበ ከብካብ መረጃዎችን የሚያስተዳድር መሆኑን ባለፈው መዘገባችን ይታወሳል።
በማ/ስ/ቅ/ ልደታ ለማርያምና ደ/መ/ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን (Lideta-EPMS) የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ (Software) በአዲስ አበባ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ የመጀመሪያ ሲሆን በሌሎች ገዳማትና አድባራትም ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ብዙዎች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ