የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን (Lideta-EPMS) የተሰኘ መተግበሪያ አበልጽጎ በሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገለጸ!!
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን Lideta Employee & Parishioners Management System (LEPMS) የተሰኘ መተግበሪያ አበልጽጎ በአዲሱ በጀት ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በደብሩ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የማኑዋል ሥራዎችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዕቅድ የተደገፈ እንቅስቃሴ ተጀምሮ አስፈላጊ ሶፍትዌሮችንና የቴክኖሎጂ መንገዶችን የሚያበለጽግ የአይሲት ክፍል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
የICT ክፍሉም በ8 ወራት ጊዜ ውስጥ Lideta Employee & Parishioners Management System (LEPMS) የተሰኘ መተግበሪያ አበልጽጎ ለሥራ ዝግጁ አድርጓል።
በዚህ መልኩ የበለጸገው ሲስተም የሠራተኞችን አጠቃላይ መረጃ በዘመናዊ እና በቀላል መንገድ ከማያስተዳድሩም ባሻገር የአስተዳደር ጽ/ቤቱን ሥራና ተግባር በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲፈጸም የሚያስችል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም የምዕመናን አጠቃላይ መረጃ የሰበካ ጉባኤ አባልነት ፣ የመዝገበ ሙታን ፣ የመዝገበ ጥምቀትና የመዝገበ ከብካብ መረጃዎችን የሚያስተዳድር መሆኑ ተወስቶ በቀጣይም የሰ/ት/ቤቱንና የደብሩን ወጣቶች እና ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎችን የሚመዘግብ ሆኖ ይታደሳል።
በዕለቱም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ኃብተወልድ ተገኝ ፣ የደብሩ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ስዩማን መሐሪ አድማሱ እና የደብሩ ዋና ሒሳብ ሹም ሊቀ ኅሩያን ሸዋንግዛው ወልደ ጻድቅ የመጀመሪያ ተመዝጋቢዎች በመሆን የምዝገባ ሥርዓቱን አስጀምረዋል።
ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ በደብሩ የአይሲቲና የስታትስቲክ ክፍሎች ጥምረት የምዕመናኑ መረጃ ወደ ዳታቤዝ ማስገባት እንደሚጀመር እና ለሌሎች የአስተዳደር ክፍሎች የሚያስፈልጉ የሶፍትዌር ግብዓቶችንም ICT ክፍሉ እንደሚያበለጽግ ከደብሩ አይሲቲ ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው