በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ተካሄደ!
ለአዲስ አበባና ለጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለ2014 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር፣
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ፣ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በርካታ ሊቃውንትና ጥሪየተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
መርሐ ግብሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀ መሆኑን መርሐ ግብሩን በመሩት በሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ መ/ር ታዴዎስ ሽፈራው ተገልጿል።
መርሐ ግብሩ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤና በሐዋርያት በኩል ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ተልእኮ የሚገልጽ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28፥1-20 ተነብቦ በጸሎት ተክፍቷል።
በንፋስ ንፋስ ላፍቶ ስልክ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር የሚገኙት፤ የጀሞ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምና የደብረ ትጉኃን ላፍቶ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሊቃውንትና የሰንበት ትምህርት ቤት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል።
በመቀጠልም ከሁለቱም አድባራት በመጡት ሁለት የቅኔ ሊቃውንት በዓሉን በተመለከተ ቅኔ ቀርቧል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰም ለብፁዕነታቸው ሰላም ላገኘንበት በዓለ ትንሣኤ የእንኳን አደረስዎ መልእክት አስተላልፈዋል።
የገዳማቱና የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች በጋራ ሆነው በመቆም ለብፁዕነታቸው እንኳን ለ2014 ዓ/ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረስዎ ብለዋል።
አያይዘውም የብፁዕነታቸውን መልካም አሠራርን አድንቀው ለወደፊትም በቃለ ዐዋዲው መሠረት ከሀገረ ስብከቱ የሚወርዱ መመሪያዎች ተቀብለው ለተፈጻሚነቱ እንደሚተጉ በጋራ ቃል ገብተዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ ለብፁዕነታቸው እንኳን ለ2014 ዓ.ም ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረስዎ ብለዋል።
ለጉባኤውም በዓሉ ትንሣኤ ልቡና ብቻ ሳይሆን ትንሣኤ ዘጉባኤም እያሰብን መሆን አለበት ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውንአስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እንኳን ለ2014 ዓ.ም ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መርሐ ግብሩን ላዘጋጁ እና በመርሐ ግብሩ ለተገኙት ሁሉ በቤተ ክርስቲያንንና በሀገረ ስብከቱ ስም አመስግነዋል።
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና ደስ ይበላችሁ በማለት ፋሲካችን በደስታና በፍቅር እያከበርን በቃሉ መሠረት መኖር አለብን ብለዋል።
ብፁዕነታቸው መጽሐፉ “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።ዮሐ14፥1-3)
እንደሚለው ትንሣኤውን ስናከብር የዘለዓለም ሕይወትን እንደምናገኝ በመተማመን፣ በሙሉ ተስፋና በደስታ መኖር እንዳለብን አስተምረዋል።
በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር ለተቸገሩ ወገኖቻችን በምንችለው ሁሉ በመደገፍና በጸሎት በማሰብ መሆንአለበት ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ