“ኒቆዲሞስ “
የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል። ስያሜውን ያገኘው እውነተኛ እውቀትንና ሕይወትን ፈልጎ ነገር ግን ምድራዊ ሥልጣኑን በአይሁድ ሸንጎ እንዳይነጠቅ ፈርቶ በሌሊት ወደ ጌታ እየሄደ ይማር ከነበረው ከአይሁድ አለቃ ከኒቆዲሞስ ነው።
ዳግም ልደትን በተመለከተ ኒቆዲሞስ የጠየቀው ጥያቄና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመለሰው መልስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ በሰፊው ተብራርቶ ተጽፏል።
ኒቆዲሞስ በፍርሃት ተውጦ እየተደበቀ በሌሊት ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲከተለው የነበረ ሲሆን በኋላ በቃሉ ተመስጦና በፍጹም ፍቅሩ ተስቦ በድፍረት ተከትሎታል። የኢየሩሳሌም ሸንጎ ኢየሱስን ሊከሰው ሲፈልግ ኒቆዲሞስ ግን መከሰስ እንደሌለበት በድፍረት ሲመሰክር እናየዋለን (ዮሐ 7፥45-52)።
በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላም ሌሎች ደቀ መዛሙርት በፍርሃት ተውጠው ሲሸሹ እርሱ ለመግነዝ የሚሆን መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ በድፍረት በቦታው ሲገኝም እንመለከተዋለን (ዮሐ 19፥39)።
የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ የሚፈልግ ሁሉ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ከውኃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ እንዳለበት የዮሐንስ ወንጌል ምዕ 3 ያስተምረናል።
ክርስቶስ ” ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው ” ብሏል። የመጀመሪያው ልደት ከእናትና አባት ከሥጋ መወለድ ሲሆን ዳግም ልደት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ የመወለድ ምሥጢር ነው። ይህ ደግሞ በሰው ኃይል ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል ነው የሚሆነው።
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረው ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገኝበት ዳግም ልደት ለእኛም ጭምር የተነገረ መሆኑን ከልብ ልናስተውል ይገባል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና ዘለዓለማዊ ነው።
ጠቅለል ባለ መልኩ ” ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው” (1ኛ ጢሞ 1፥15) ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረው ክርስቶስ የከፈለልንን የደም ዋጋ ከልብ በማመንና ዘወትር ያለማቋረጥ ፍቅሩንና ቤዛነቱን በማሰብ በፍርሃትና በሌሊት ሳይሆን በፍጹም እምነትና በብርሃን ልንከተለው ይገባል።
የዳግም ልደት ዋናው ጽንሰ ሃሳብም ለምድራዊው ሥልጣንና ሀብት ቅድሚያ በመስጠት በሥጋ ልደት ጸንቶ መኖር ሳይሆን ለዘለዓለማዊ ሕይወት ቅድሚያ በመስጠት ዳግም ከመንፈስ ቅዱስ በመወለድ ሰማያዊ ዜግነትን ማግኘት ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ