በፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተ ክርስቲያን ለሚያገለግሉ ማኅበረ ካህናት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል!!
በጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተክርስቲያን ለሚያገለግሉ ማኅበረ ካህናት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ዘማርያም ሙጬ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ሥልጠና የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
አያይዘውም የዚህ ሥልጠና ዋና ዓላማ የደብሩ ካህናትን በሥልጠና ብቁ በማድረግ የወንጌል አገልግሎትን በሰፊው ለምእመናን በማድረስ ለመንግሥቱ ማዘጋጀት እንደሆነ ገልጸዋል።
የን/ስ/ላ/ክ/ ከተማ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል ኃላፊ በኩረ ትጉኃን ደመላሽ ቶጋ በመርሐ ግብሩ መግቢያ ላይ ትምህርተ ኖሎትን አስመልክተው ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
ካህናት በእግዚአብሔር ለአገልግሎት የተመረጡ መሆናቸውንና ለተሾሙለት አገልግሎት ታማኝ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዋናነት የዛሬውን ሥልጠና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የኒዎርክና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው “አገልጋይነት” በሚል ርዕስ ሰፊ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በርካታ ተያያዥ ጉዳዮችንም አንስተዋል።
አገልጋይ ከምንም በፊት ማንን እንደሚያገለግል፣ ለምን እንደሚያገለግልና ስለ አገልጋይነት ሕይወት ጠንቅቆ ሊረዳና በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ አገልጋይነት ማለት ራስን መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ፣ ለዕረፍት ተጠርቶ ላሳረፈው አምላክ በትጋት መሥራትና ራስን ለሌላ አሳልፎ መስጠት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አክለውም ሌላውን በፍጹም ልብና ፈቃድ ማገልገል፣ ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለመንጋው መሥራት፣ ምእመናንን መመገብና መጠበቅ፣ በክርስቶስ መወደዱን አውቆና ተረድቶ ሌሎችን መውደደና መጠበቅ እንዲሁም በትጋት ማስተማር የአገልጋይነት ሕይወት መሆኑን አብራርተዋል።
አገልጋይ ዘወትር ያለ ድካም በእውቀት፣ በእምነትና በመታዘዝ ማደግ እንዳለበት ግንዛቤ አስጨብጠዋል።
የአገልግሎት ግብም ምእመናን ለመንግሥቱ ማብቃትና እግዚአብሔርን ማክብር እንደሆነ ገልጸዋል።
እውነተኛ መሆን፣ አውቆ መገኘት፣ በእምነት መመላለስ የአገልጋይ መንፈሳዊ መሣሪያዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
የአገልጋይ ባህርይም ምን መምሰል እንዳለበት የጠቀሱ ሲሆን ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ ትዕግስትና አርቆ ማየት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ዘወትር የማያነብና ለማወቅ የማይጥር አገልጋይ የቤተክርስቲያን ዕዳ ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
አያይዘውም አንድ አገልጋይ ራሱን እንደ ሊቅ ሳይሆን ዘወትር እንደተማሪ ማየት አለበት፤ በማንበብም ራሱን ማሳደግ ይኖርበታል ብለዋል።
በአገልጋይነት ሕይወት ውስጥ በአእምሮ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በልብ መረዳትም ጭምር እንዳለ ጠቅሰዋል።
ቅዱሱ መጽሐፍ ” ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው “(1ኛ ጢሞ 1፥15) እንደሚል ጠቅሰው አንድ አገልጋይ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኒትነት ለዓለም መመስከር አለበት በማለት ተናግረዋል።
ሁሉም አገልጋይ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መንፈሳዊና መለኮታዊ አደራ በፍቅር ሊወጣ ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
መ/ገ ዘማርያም ሙጬ ብፁዕነታቸው ደብሩ ድረስ በመገኘት ለደብሩ ማኅበረ ካህናት ለሰጡት ሥልጠና ከልብ አመስግነዋል።
ሥልጠናው በነገው ዕለትም “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” በሚል ርዕስ የሚቀጥል መሆኑን አሳስበዋል።
ክቡር አስተዳዳሪው የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናው እንዲሰጥ መልካም ፈቃዳቸው በመሆኑ አመስግነዋል።
ወደፊት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት ሥልጠና እንደሚሰጥም ክቡር አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለን/ስ/ላ/ክ/ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤትም ምስጋና አቅርበዋል።
የደብሩ ዋና ጸሐፊ መልኬ ታደሰ ከምንም በላይ ለሥልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ ፊት የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ሰፋ ባለ መልኩ ደብሩ እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ጨምሮ የን/ስ/ላ/ክ/ ከተማ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል ኃላፊ በኩረ ትጉኃን ደመላሽ ቶጋ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መ/ገ ዘማርያም ሙጬ፣ የደብሩ የአስተዳደር ሠራተኞችና የደብሩ ማኅበረ ካህናት ተግኝተዋል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ (ፎቶ)